በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችንና ስነ ምህዳርን መሰረት ያደረገ ተከላ ለማካሄድ ዝግጅት ተደርጓል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 7/2017(ኢዜአ)፦ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችንና ስነ ምህዳርን መሰረት ያደረገ ተከላ ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ።

በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም መሪ ስራ አስፈፃሚ ፋኖሴ መኮንን ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ በዘንድሮው ክረምት ለሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በቂ ዝግጅት ተደርጓል።

በመርሃ ግብሩ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ መትከል የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ገልጸው፤ ለሀገር በቀልና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ላላቸው ችግኞች ትኩረት መሰጠቱንም ጠቁመዋል።


 

የችግኝ ተከላ ሂደቱም ስነ-ምህዳርን መሰረት ያደረገ እንደሚሆን ጠቅሰው፤ ለዚህም አስፈላጊ የሆኑ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

ባለፉት አመታት ከተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሮች ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶች መገኘታቸውን ያነሱት መሪ ስራ አስፈጻሚው ይህም አሁን ላይ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ርብርብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እና የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል። 


 

የጉለሌ እጽዋት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጉተማ ሞረዳ በበኩላቸው፤ አዲስ አበባ ከተማን ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ  የአረንጓዴ አካባቢ ሽፋንን ማሳደግ ወሳኝ ነው።

ይህም የአየር ብክለትን ለመከላከል ጉልህ ሚና እንዳለው አንስተው፤ ለዚህም ሀገር በቀል እጽዋት ተመራጭ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርም በማዕከሉ ከተዘጋጁት ችግኞች 50 በመቶ የሚሆኑት ሀገር በቀል ዝርያ ያላቸው ናቸው ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም