የወጣቶችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የልማት ተግባራትን ይበልጥ ማጠናከር ይገባል - ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀስላሴ

ጊንጪ፤ ሰኔ 7/2017(ኢዜአ)፦ የወጣቶችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የልማት ተግባራትን ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀስላሴ ገለጹ።

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ጊንጪ ከተማ አቅራቢያ የተገነባው 'ኬኛ ቢቨሬጅስ' ፋብሪካ ዛሬ ተመርቆ አገልግሎት ጀምሯል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓት ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀስላሴ፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሸመልስ አብዲሳን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።


 

በዚህ ወቅት ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀስላሴ፤ የልማት ስራዎች የወጣቱን ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረጉ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ዛሬ የተመረቀው ፋብሪካም ለአካባቢው ማህበረሰብ ትልቅ በረከት መሆኑን ጠቅሰው፤ ከጥሬ እቃ አቅርቦት ጀምሮ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አለውም ብለዋል።

በተለይ የግብርና ዘርፉን ከማሳደግ አንጻር ፋይዳው የጎላ መሆኑን አንስተዋል።

ይህም በመሆኑ ለወጣቶች ስራ የሚፈጥሩ እና የወጣቱን ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረጉ የልማት ተግባራትን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።


 

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው፤ በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የልማት ተግባራት ወጣቶችን በስፋት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት አሰራሮችን በማሻሻል እና ህዝቡን በስፋት በማሳተፍ አበረታች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

በክልሉ ያለውን የልማት አቅም በመጠቀም የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አንስተዋል።

በተለይም ወጣቶች ስራ እንዲያገኙና በንቃት እንዲሳተፉ ዕድል የፈጠሩ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ዛሬ የተመረቀው ፋብሪካ የዚሁ ጥረት ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፤ መሰል ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

ፋብሪካው በክልሉ ምዕራብ ሸዋ ዞን በ110 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፤ 22 ቢሊዮን ብር ኢንቨስት የተደረገበት መሆኑም ታውቋል።

ፋብሪካው ከ4ሺህ በላይ ባለአክሲዮኖች የተቋቋመ፣ ከ250 ለሚበልጡ ዜጎች የስራ ዕድል ያገኙበትና እና በእሴት ሰንሰለቱ መሰረት ለ1ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥር ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም