የሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት በሌሎች ተቋማት እንደ አርዓያ የሚወሰድ ተግባር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት በሌሎች ተቋማት እንደ አርዓያ የሚወሰድ ተግባር ነው

ሰኔ 7/2017(ኢዜአ)፦ የሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት በሌሎች ተቋማት እንደ አርዓያ የሚወሰድ ተግባር እያከናወነ መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ እና ፍትህ ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ኢሳ ቦሩ አመለከቱ።
የሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት በ2017 በጀት ዓመት ባከናወናቸው ውጤታማ ተግባራትና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በተመለከተ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ እና ፍትህ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ውይይት አድርጓል።
በውይይቱም የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ኢሳ ቦሩ እንዳሉት፣ የሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህም ተገልጋዩ ጥራት ያለው አገልግሎት እያገኘ መሆኑን ጠቁመው በተለይም ከለውጡ በፊት የአገልግሎት ሰጪ ተቋማቱ የህዝብ እሮሮ የሚሰማባቸውና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር የሚስተዋልባቸው እንደነበሩ አስታውሰዋል።
ሆኖም የለውጡ መንግስት በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ በወሰደው የማሻሻያ ሪፎርሞች ስራዎች በርካታ ለውጦች መታየታቸውን ጠቁመዋል።
በዚህም በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት በመስጠት ለሌሎች ተቋማት እንደአርዓያ የሚወሰድ አገልግሎት እንዲሰጥ ምክንያት መሆኑን አንስተዋል።
የሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሃሚድ ኪኒሶ በበኩላቸው፣ ተቋሙ ከምንጊዜውም በላይ አገልግሎቱን እያሰፋ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ለዚህም ተቋሙ ዘመኑን የዋጁ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ጥቅም ላይ በማዋል ረጅም ወረፋ በመያዝ ለደንበኞች እንግልት ይፈጥር የነበረውን አሰራር በኦንላይን በማድረግ የተገልጋዩን እርካታ መጨመር መቻሉን ገልፀዋል።
በዚህም በቀን በአማካይ ከስድስት ሺህ በላይ ደንበኞችን እንደሚያስተናግድ ገልፀው ከመንግሥት የስራ ሰዓት ውጪ የምሳ ሰዓትን እንዲሁም እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት አገልግሎቶች እየተሰጡ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ፣ ሀሰተኛ ሰነዶችን የሚያጋልጡና የተለያዩ የማጭበርበር ተግባራትን መከላከል የሚያስችሉ የተለያዩ አዳዲስ አሰራሮች ወደ ትግበራ መግባታቸውንም አብራርተዋል።
የፋይዳ መታወቂያን እንደ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጣችን ማንነትን መሰረት ተደርጎ ይሰራ የነበረውን ማጭበርበር ማስቀረት ተችሏል ብለዋል።