በብሔረሰብ አስተዳደሩ በ71 ትምህርት ቤቶች የጓሮ አትክልት ልማት የሰርቶ ማሳያ ተግባር እየተከናወነ ነው

ሰቆጣ ፤ሰኔ 7/2017 (ኢዜአ)፡- በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በ71 ትምህርት ቤቶች ስርዓተ ምግብን ለማጎልበት የሚያስችሉ የጓሮ አትክልት ልማት ሰርቶ ማሳያ እየተከናወነ መሆኑን የብሔረሰብ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ፍትሃለሽ ምህረቴ ለኢዜአ እንደገለፁት በብሔረሰብ አስተዳደሩ የሚስተዋለውን የስርዓተ ምግብ ችግርን ለመቅረፍ ሁሉን አቀፍ ጥረት እየተደረገ ነው።

በዚህም በትምህርት ቤቶች ላይ የምገባ መርሃ ግብር በማካሄድ ህጻናት በቂ ምግብ አግኝተው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉና ውጤታማ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በ71 ትምህርት ቤቶች የስርዓተ ምግብ የጓሮ አትክልት ልማት በማካሄድ የስርዓተ ምግብ ችግርን ለመቅረፍ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። 

በትምህርት ቤቶች እየተካሄደ ያለው የጓሮ አትክልት ልማት ክበባትን በማቋቋም ተማሪዎች በቀጣይ በቤታቸውም እንዲተገብሩት ግንዛቤ መፍጠር ጀምሮ ሌሎች እገዛዎች እየተደረጉ ነው ብለዋል። 

የትምህርት ቤቶች ባላቸው ክፍት መሬት ተጠቅመው የጓሮ አትክልት በማልማት ለማህበረሰቡ ሞዴል በመሆን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሚፈጥረውን ችግር ለመቅረፍ አልመው መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።


 

በዞኑ በጋዝጊብላ ወረዳ የመስቀሎ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ስለሽ ጌታሁን እንዳሉት በትምህርት ቤታቸው እየተከናወነ ያለው የአትክልት ልማት ለሌላው ማህበረሰብ እንደ ተሞክሮ የሚወሰድ ነው።

ወደ ማህበረሰቡ ለማስፋትም 30 ተማሪዎች አባል የሆኑበት የስርዓተ ምግብ ክበብ በመመስረት የጓሮ አትክልት ልማትን በቤታቸውና በአካባቢያቸው እንዲያካሄዱ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 


 

በትምህርት ቤቱ የስርዓተ ምግብ ክበብ አባል የሆነችው ተማሪ ጤና ታደሰ፤ በትምህርት ቤቱ በክበባቸው አማካኝነት የጓሮ አትክልት እያለሙ መሆናቸውን ተናግራለች። 

''ክበቡ የስርዓተ ምግብ ግንዛቤን ከማስጨበጥ ባለፈ በቤታችን የጓሮ አትክልትን በማልማት እንድንመገብ አስችሎናል።'' ብላለች።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም