ኢትዮጵያ ስደተኞችን በተመለከተ የምትከተለው አካታች መርሃ ግብር በአርአያነት የሚወሰድ ነው - የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ስደተኞችን በተመለከተ የምትከተለው አካታች መርሃ ግብር በአርአያነት የሚወሰድ ነው - የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 7/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ስደተኞችን በተመለከተ የምትከተለው አካታች መርሃ ግብር በአርአያነት ሊወሰድ የሚችል መሆኑን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ ተናገሩ።
የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ስደተኞችን በአካታችነት መደገፍን የተመለከተ ከፍተኛ የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ አካሂዷል።
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በስደተኞች ዙሪያ እየተገበረችው ያለው ፖሊሰ የሚደነቅ ነው።
በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎችን በጎበኙበት ወቅት የተሻለ አገልግሎት እየተሰጣቸው መሆኑን ማረጋገጥ ችያለሁ ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ስደተኞችን ታሳቢ ያደረገ አካታች መርሃ ግብር ተግባራዊ በማድረግ በትምህርት፣ በጤና፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በዲጂታል አካታችነትና ሌሎች አገልግሎቶች ተጠቃሚ አድርጓል ነው ያሉት።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ስደተኞችን በተመለከተ የምትከተለው አካታች መርሃ ግብር ሌሎች ሀገሮችም በአርአያነት በመውሰድ ሊያሰፉት የሚገባ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት።
ስደተኞች በአካታች መርሃ ግብሮች በምጣኔ ሃብት ውስጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ በዘላቂነት እራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ሰብዓዊ ድጋፍን መቀነስ በመሆኑ የሚበረታታ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በሯን ክፍት አድርጋ ስደተኞችን በመቀበል በአካታችነት ለማስተናገድ እያከናወነችው ያለውን ተግባር አለም አቀፍ ማህበረሰብ ሊደግፍ እንደሚገባ በአጽንኦት አንስተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ የረጅም ጊዜ ታሪክ አላት።
ስደተኞችን በአካታችነት በመቀበል የጤና፣ የትምህርትና ሌሎች አገልግሎቶችን በመስጠትና በምጣኔ ሃብት በዘላቂነት ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ በፖሊሲ ደረጃ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች እንደምትገኝ አስረድተዋል።
በተመሳሳይ መሰረታዊ በሆኑ አገልግሎቶች በወሳኝ ኩነት እንዲሁም ዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል።
በትምህርት ዘርፍ በመጀመሪያ ደረጃ፣ በቴክኒክና ሙያ እንዲሁም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ችላለች ብለዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ፤ በምጣኔ ሃብት ዘርፍም በስራ ዕድል ፈጠራ በማካተት በዘላቂነት ራሳቸውን የሚችሉበት ዕድል የተፈጠረ ሲሆን፤ አብዛኞቹ ስደተኞች ይህን ዕድል እየተጠቀሙበት መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ስደተኞችን ታሳቢ ያደረገ የተቀናጀ እና አካታች አሰራሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሃሰን እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞችን ተቀብላ እያስተናገደች ትገኛለች።
ስደተኞችን በአካታችነት በመደገፍ በቀጣይ የትምህርት፣ የጤና፣ የኢንተርኔት ተደራሽነትና ሌሎች አገልግሎቶችን የበለጠ ለማጠናከርም ይሰራል ብለዋል።
መንግስት በዘላቂነት ስደተኞች ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ እየተገበራቸው ላሉ የተለያዩ መርሃ ግብሮች ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የቴክኒክና የገንዘብ ትብብሩን ሊያጠናክር ይገባል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የተ.መ.ድ ዋና ተጠሪና የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ ራሚዝ አልካባሮቭ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ለስደተኞች ሁልጊዜም በሯን ክፍት በማድረግ የምትቀበል ሀገር ናት ብለዋል።
በመሆኑም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በጀቱን በማሳደግ መንግስት እያከናወነ ያለውን ተግባር ሊደግፍ ይገባል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ተግባራዊ እያደረገችው የሚገኘውን አካታች መርሃ ግብር እንደሚደግፉ በመድረኩ የተገኙ የተለየዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ አለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አረጋግጠዋል።