ሴቶች በግንባታ ዘርፍ ያለውን እድልና ቴክኖሎጂ በመጠቀም ወደ ዘርፉ በስፋት እንዲገቡ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ሴቶች በግንባታ ዘርፍ ያለውን እድልና ቴክኖሎጂ በመጠቀም ወደ ዘርፉ በስፋት እንዲገቡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 7/2017(ኢዜአ)፦ ሴቶች በግንባታ ዘርፍ ያለውን እድልና ቴክኖሎጂ በመጠቀም ወደ ዘርፉ በስፋት እንዲገቡ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ጥሪ አቀረበ።
ኮርፖሬሽኑ ”ኢትዮጵያ ትገንባ” በሚል መሪ ሀሳብ ሴቶች በኮንስትራክሽን ዘርፉ ያላቸው ተሳትፎ በሚዳብርበት ሁኔታ ላይ የሚመክር ኮንፍረንስ እያካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሴት አመራሮች እንዲሁም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት አመራሮች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ፅህፈት ቤት ሃላፊ ቤዛዊት ግርማ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኮርፖሬሽኑ ሴቶች በዘርፉ ያላቸውን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ በተለያዩ ህጎች ላይ ማሻሻያዎች በማድረግና ስትራቴጂዎችን በመንደፍ እየተሰራ ይገኛል።
ኮርፖሬሽኑ ተግባራዊ ካደረጋቸው የሪፎርም ስራዎች መካከልም ስርዓተ ፆታን ማካተትና የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ አንዱ መሆኑን አንስተዋል።
በተጨማሪም ሴቶችን ያማከሉ የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች በመስጠትና የትምህርት ዕድል በማመቻቸት የማብቃት ስራዎች እንደተሰሩም ተናግረዋል።
ሴቶች በግንባታ ዘርፍ ያለውን እድልና ቴክኖሎጂ በመጠቀም እውቀታቸውንና ክህሎታቸውን ይበልጥ በማዳበር ወደ ኮንስትራክሽን ዘርፉ በስፋት እንዲገቡም ጠይቀዋል።