የከተማዋ ነዋሪዋች በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በመሰማራት ተጠቃሚ ሆነዋል

ቡታጅራ ፤ሰኔ 7/2017 (ኢዜአ)፡-በቡታጅራ ከተማ አስተዳደር በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በእንስሳት እርባታና በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ላይ በመሰማራት ተጠቃሚ  መሆናቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ ።

የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት ትኩረት እንደተሰጣቸው ነው ያመለከተው።


 

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት "የእኛ ለእኛ የወተት እርባታ ማህበር" ሰብሳቢ አቶ ሳህሌ መኮንን እንደገለጹት፤ ለአምስት ተደራጅተው በሁለት የወተት ላሞች ስራ ከጀመሩ ሁለተኛ ዓመት እንደሆናቸውና የተሻለ ገቢ ወደ ማግኘት እየተሸጋገሩ ነው ።

አስተዳደሩ ባመቻቸው የመስሪያ ቦታና መነሻ ብድር እና የህይወት ክህሎት ስልጠና በመታገዝ ገቢያቸው እያደገ መምጣቱን ተናግረው ማህበሩ ከአባላቱ ጥቅም አልፎ ለሌሎች የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ መጀመሩን ገልጸዋል።


 

ሌላኛውና ለሶስት ተደራጅተው በእንቁላልና ስጋ ዶሮ እርባታ ስራ ላይ የተሰማሩት "የቤተሰብ የዶሮ እርባታ ማህበር" ሰብሳቢ  ኡስማን ሳቢር በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በተደረገላቸው ድጋፍ  ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

በአሁኑ ወቅትም የእንቁላልና የሥጋ ዶሮዎችን በማርባት ለገበያ በማቅረብ ውጤታማ እየሆኑ እንደሚገኙና የገበያ ትስስር እንደተፈጠረላቸውም አስረድቷል። 

ከዚህም ባለፈ ባላቸው ውስን ቦታ አትክልት እና ፍራፍሬ እያለሙ መሆኑን ገልፀው በስራቸው ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል።


 

መምህር ጀንበር ፈለቀ በበኩላቸው ከሌሎች ባገኙት ልምድ ከመምህርነት ሙያቸው ጎን ለጎን ፍየልና በግን በማሞከት ተግባር ላይ ተሰማርተው ህይወታቸውን እየቀየሩ ነው።

የቡታጅራ ከተማ ከንቲባ አቶ አብዱ አህመድ በበኩላቸው በከተማዋ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ተደራጅተው የተሰማሩ ዜጎች ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረው ዘርፉን ለማጠናከርም መንደር የመፍጠር ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በከተማዋ 23 የዶሮ፣ 21  የወተት እንዲሁም 3 የንብ  መንደሮች መፈጠራቸውን ከንቲባው አውስተዋል።


 

በማህበር በመደራጀት በተቀናጀ መንገድ ወደ ስራ የገቡ ዜጎች በሚደረግላቸው ድጋፍ ታግዘው ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የስራ ዕድል እየፈጠሩ እንዳሉም ጠቁመዋል።

ይህን  ለማጠናከርም የብድር፣ የቦታና የክህሎት ማሳደጊያ ስልጠና ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ ነው ብለዋል ከንቲባው።

እንዲሁም ዝርያቸው የተሻሻሉ የወተት ላሞች፣ ዶሮ እና የአሳ ጫጩት በዘርፉ ለተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሰራጩ  መሆናቸውን አመልክተዋል።

በተጨማሪም የማር ምርት ለማሳደግ ዘመናዊ ቀፎዎችን የማቅረብ ስራም እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የሌማት ትሩፋት ከኢኮኖሚ ምንጭነት፣ ከምግብ ፍጆታነትና ገበያን ከማረጋጋት ባለፈ በስነ-ምግብ ረገድ እየተጫወተ ያለውን ጉልህ ሚና ለማጠናከር የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም