በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 2ሺህ 500 ቤቶችን ለመገንባት እቅድ ተይዟል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 7/2017(ኢዜአ)፦ በ2017 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 2 ሺህ500 ቤቶችን ለመገንባት እቅድ መያዙን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2017 የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መክፈቻ መርኃ-ግብር ተካሂዷል።

በመርኃ ግብሩ ማስጀመሪያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽነር ይመር ከበደ እና የአስተዳደሩ ከፍተኛ  የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።


 

ከንቲባ አዳነች በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባህል ሆኖ መቀጠል ያለበት መልካም ተግባር ነው።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በከተማዋ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችንና ባለሃብቶችን በማስተባበር የበጎ ሥራ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።

በ2017 የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በርካታ ሰው ተኮር ተግባራት እንደሚፈጸሙ ገልጸው፤ 18 የተለያዩ በጎ ፈቃድ ተግባሮችን ለመተግበር መታቀዱን አብራርተዋል።

ከተማዋን ምቹ እና ለኑሮ ተስማሚ እንድትሆን የሚያስችሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች እንደሚከናወኑ ከንቲባዋ ገልፀዋል።


 

በዚህ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርኃ ግብር 2 ሺህ 500 ቤቶችን በ90 ቀናት ለመገንባት መታቀዱንም ነው የገለጹት።

በተጨማሪም 500 ሺህ ለሚሆኑ ለከተማዋ ነዋሪዎች በድግግሞሽ ማዕድ የማጋራት ዕቅድ መያዙንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም