የመጀመሪያው የፊፋ ክለቦች የዓለም ዋንጫ ዛሬ ይጀመራል

አዲስ አበባ ሰኔ 7/2015(ኢዜአ):- የመጀመሪያው የፊፋ ክለቦች የዓለም ዋንጫ በአሜሪካ አስተጋጅነት ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳል።

በምድብ አንድ የሚገኙት አል አህሊ ከኢንተር ሚያሚ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት በሚያሚ ሀርድ ሮክ ስታዲየም የመክፈቻ ጨዋታውን ያደርጋሉ።

እ.አ.አ በ2000 የተጀመረው ውድድር (ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ) ከዚህ ቀደም አህጉራዊ የክለቦች ውድድርን ያሸነፉ ክለቦች የሚሳተፉበት ነበር።

ዓለም አቀፉ የፊፋ በአዲስ መልክ ባስተዋወቀው አሰራር መሰረት ነባሩን ፎርማት በመሻር የተሳታፊ ክለቦችን ቁጥር ወደ 32 አሳድጓል።

በዚሁ መሰረት ቡድኖቹ በስምንት ምድብ ተከፍለው ለአራት ሳምንታት 63 ጨዋታዎች በ11 የአሜሪካ ከተሞች ያደርጋሉ።

በምድብ አንድ አል አህሊ፣ ኢንተር ሚያሚ፣ ፓልሜራስ እና ፖርቶ፣  በምድብ 2 አትሌቲኮ ማድሪድ፣ ቦታፎጎ፣ ፒኤስጂ እና ሲያትል ሳውንደርስ፣  በምድብ 3 ኦክላንድ ሲቲ፣ ባየር ሙኒክ፣ ቤኔፊካ እና ቦካ ጁኒየርስ፣  በምድብ 4 ቼልሲ፣ ኤስፔራንስ፣ ፍላሚንጎ እና ሎስ አንጀለስ ኤፍሲ ይገኛሉ።


 

በምድብ አምስት ሪቨር ፕሌት፣ ኡርዋ ሬድ ዳይመንድስ፣ ሞንትሬይ እና ኢንተር ሚላን፣ ምድብ 6 ፍሉሜንሴ፣ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ፣ ኡልሳን እና ማሜሎዲ ሳንዳውንስ፣  ምድብ 7 ማንችስተር ሲቲ፣ ዋይዳድ ካዛብላንካ፣ አል አይን እና ጁቬንቱስ፣ በመጨረሻው ምድብ 8 ሪያል ማድሪድ፣ አል ሂላል፣ ፓቹካ እና ሬድ ቡል ሳልበዝርግ ተደልድለዋል።

በክለቦች የዓለም ዋንጫ ላይ ከአውሮፓ፣ ደቡብ አሜሪካ፣ ሰሜን አሜሪካ፣ አፍሪካ ፣ ማዕከላዊ አሜሪካ፣ ካሪቢያን እና ኦሺንያ ቀጣናዎች የሚገኙ ክለቦች ይሳተፋሉ።

ፊፋ አህጉራት ባላቸው ወቅታዊ ብቃት እና ውጤት መሰረት ለአውሮፓ 12 (ዩኤፋ) ፣ ለደቡብ አሜሪካ  (ኮንቤሞል) ስድስት፣ እስያ (4(፣ አፍሪካ (4) እና ሰሜን አሜሪካ ፣ ማዕከላዊ አሜሪካ እና ካሪቢያን (ኮንካካፍ) በተመሳሳይ አራት አግኝተዋል።

አሜሪካ በአዘጋጅነቷ እና ኦሽንያ ባላት አህጉራዊ የክለብ ውጤት በተመሳሳይ አንድ አንድ የተሳትፎ ኮታ አግኝተዋል።

ፊፋ ለውድድሩ ተሳታፊዎች የአንድ ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሽልማት አዘጋጅቷል።

የፊፋ ክለቦች የዓለም ዋንጫ እስከ ሐምሌ 6 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም