የኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ 50ኛው የፕሪሚየር ሊግ የደርቢ ጨዋታ ይጠበቃል

አዲስ አበባ ሰኔ 7/2015(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ35ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በሚያደርጉት ተጠባቂ ጨዋታ ዛሬ ይጀመራል።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከቀኑ 9 ሰዓት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይካሄዳል።

በደረጃ ሰንጠረዡ ኢትዮጵያ ቡና በ55 ነጥብ 2ኛ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ45 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

በአሰልጣኝ ነጻነት ክብሬ የሚመራው ኢትዮጵያ ቡና በፕሪሚየር ሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው 32 ጨዋታዎች 16 ጊዜ ሲያሸንፍ 8 ጊዜ ተሸንፎ፤ 8 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይቷል።

በ32ቱ ጨዋታዎች 28 ግቦችን ሲያስቆጥር 16 ጎሎችን አስተናግዷል።


 

ተጋጣሚው ቅዱስ ጊዮርጊስ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው 32 ጨዋታዎች በ12ቱ አሸንፎ 11 ጊዜ ተሸንፏል። 9 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በፕሪሚየር ሊጉ እርስ በእርስ ሲገናኙ የዛሬው ለ50ኛ ጊዜ ነው።

ከዚህ ቀደም 49 ጊዜ ተጫውተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 21 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ ኢትዮጵያ ቡና 8 ጊዜ ድል ቀንቶታል። 20 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

በ45ቱ ጨዋታዎች በድምሩ 95 ጎሎች የተቆጠሩ ሲሆን ፈረሰኞቹ 63 እንዲሁም ቡናማዎቹ ደግሞ 32 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

ኢትዮጵያ ቡና የሊጉን ዋንጫ አንድ ጊዜ ያነሳ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ 16 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል።

በሊጉ ኢትዮጵያ ቡና መልካም የሚባል ጊዜን ያሳለፈ ሲሆን በአንጻሩ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሚፈለገው የብቃት ደረጃ ላይ አልተገኘም።

የሁለቱ ክለቦች በርካታ ደጋፊዎች ለጨዋታው ድምቀት ይሰጡታል ተብሎ ይጠበቃል።

ቡድኖቹ በመጀመሪያው ዙር በሊጉ ባደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ አቻ መለያየታቸው የሚታወስ ነው።

ምሽት 12 ሰዓት ሻምፒዮንነቱን አስቀድሞ ያረጋገጠው ኢትዮጵያ መድን ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ይጫወታሉ።

ኢትዮጵያ መድን በ67 ነጥብ የሊጉ አናት ላይ ሲቀመጥ ሀድያ ሆሳዕና በ47 ነጥብ 5ኛ ደረጃን ይዟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም