መንግስት ያደሩ ችግሮችን በአምስት ማዕቀፍ ለመፍታት ወስኖ እየሰራ ይገኛል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 7/2017(ኢዜአ)፦ መንግስት ያደሩ ችግሮችን በአምስት ማዕቀፍ ለመፍታት በመወሰን እየሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከመላው ኢትዮጵያ ከተውጣጡ መምህራን ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱም ከመምህራን ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም የመምህራንን ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተው ነገር ግን ጥያቄው በደሞዝ ጭማሪ ብቻ የሚመለስ አለመሆኑን አብራርተዋል።

መንግስት ያደሩ ችግሮችን በአምስት ማዕቀፍ ለመፍታት ወስኖ እየሰራ መሆኑን ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጀመሪያው አካታች ሀገራዊ ምክክር መሆኑንና ይህም በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው እንደሆነ አስታውሰዋል።


 

እንዲሁም የሽግግር ፍትህ፣ የታጠቁ አካላትን በተሐድሶ መልሶ ወደ ህብረተሰቡ መቀላቀል(ዲዲአር)፣ የብዝሀ ዘርፍ የኢኮኖሚ ሪፎርም እና የተቋማት ሪፎርም ሌሎች ማዕቀፎች መሆናቸውን አብራርተዋል።

በሌላ በኩል የትምህርት ዘርፋን በጀት በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ፣  የአንድ ዩኒቨርሲቲ በጀት ከትምህርት ሚኒስቴር በጀት እንደሚበልጥና የእያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ በጀት ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

መምህራን ማሰብ ያለባቸው ገበታውን እንዴት እናስፋው የሚለውን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገበታ ለማስፋት ምርታማነት ላይ በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ተቋማትን በማዘመን የመምህራንን ጥያቄ ለመመለስ ይሰራልም ነው ያሉት።


 

የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ፣ የጋራ ትርክት ግንባታ፣ ምርታማነት፣ የገጠር ኮሪደር እና የትምህርት ጥራት ላይ በጋራ መረባረብ እንደሚያስፈልግ አውስተዋል።

ችግሮችን ለመፍታት የተቀመጡ አምስቱ ማዕቀፎችም አድራሽ እንጂ ግብ አይደሉም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለስኬቱ ሁሉም እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም