መምህራን እውነትና እውቀትን መለኪያ በማድረግ በትውልድ እና በሀገር ግንባታ ላይ የመሪነት ሚናቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
መምህራን እውነትና እውቀትን መለኪያ በማድረግ በትውልድ እና በሀገር ግንባታ ላይ የመሪነት ሚናቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2017(ኢዜአ)፦ መምህራን እውነትና እውቀትን መለኪያ በማድረግ በትውልድ እና በሀገር ግንባታ ላይ የመሪነት ሚናቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አስገነዘቡ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከመላው ኢትዮጵያ ከተውጣጡ መምህራን ጋር ውይይት አካሂደዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመምህራን ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ፤ መምህራን በእውቀትና እውነት ላይ የተመሰረቱ በመሆናቸው ሀሳባቸው ለፖሊሲ ግብዓትነት እንደሚውል ተናግረዋል፡፡
የአያት እና ቅድመ አያቶቻችን ዘመን የተለያዩ እንደነበሩ ጠቅሰው፤ የእኛ ዘመን ደግሞ የተለየ ዓለም መሆኑን መረዳት ይገባል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ እውቀትና እውነት መለኪያ እንዲሆኑ መምህራን ተግተው መስራት አለባቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁን ያለውን ለማሳነስ የሌለ ድሮ ማንሳት እንደማይገባ ገልጸዋል፡፡
እውነትና እውቀት ፈታኝና ዋጋ የሚያስከፍሉ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ብዙዎች የጥፋት አካሄድ የሆነውን ቀላሉንና አቋራጭ መንገድ ይከተላሉ ብለዋል፡፡
አሁን ያለንበት የድህረ እውነት ዘመን ውሸትና ጩኸት የነገሰበት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አለመስራት ብቻ ሳይሆን የተሰራ እንደሚያፈርስ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም መምህራን ከባዱንና ፈታኝ የሆነውን እውነትና እውቀት በመፈለግ ትውልድ ማሻገርና ሀገር መገንባት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
የመምህራን ተሰጥኦ መድከም፣ መስራትና ሀገር ማሻገር በመሆኑ ከእለት ጉርስ አልፎ ማሰብ የሚችል ትውልድ ሊፈጥሩ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ለልጆቻችን የተሻለች ሀገር ለማውረስ ድህነት በቃን፣ ልመና ሰለቸን ብለን ጥሪታችንን አሟጠን ልማት ላይ ማዋል ይገባናል ብለዋል፡፡
በዚህ ስሜት በገነነበት፣ እውነት በኮሰመነበት ዘመን መምህራን እውነትና እውቀት የሚገዳቸው እንጂ ዘረኝነት የሚያስጨንቃቸው ሊሆኑ አይገባም ነው ያሉት፡፡
መምህራን የትናንትን ታሪክ እና የዛሬውን ነባራዊ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን የመጪውን ዘመን ደረጃ ጭምር መገንዘብ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡