መምህራን በድህረ እውነት ዘመን እውቀት እና እውነት እንዲነግሱ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2017(ኢዜአ)፦ መምህራን በድህረ እውነት ዘመን እውቀት እና እውነት ነግሰው እንዲወጡ የማድረግ ወሳኝ ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከመላው ኢትዮጵያ ከተውጣጡ መምህራን ጋር ተወያይተዋል።

 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አሁን ያለንበት ዘመን ውሸት እና ጩኸት የነገሰበት ነው፤  ውሸት እና ጩኸት ደግሞ የተሰራ ነገር ያፈርሳል ብለዋል። 


 

የድህረ እውነት ዘመን መዳረሻ አላማ እና ግብ የሌለው ከዕለት ጉርስ ያለፈ ነገር ማየት የማይችል ትውልድ መፍጠር መሆኑን አመልክተዋል።  

ይህም ከምክንያታዊነት እና እውነታ ይልቅ ስሜታዊነት ይበልጥ እንዲጎላ የሚያደርግ እንደሆነም ነው የተናገሩት።

መምህራን በዚህ የድህረ እውነት ዘመን እውነት እና እውቀት አሸንፈው እንዲወጡ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡም አስገንዝበዋል። 

መምህራን የትናንት ታሪክን በማወቅ፣ ዛሬ በመረዳትና ነገን በመገንዘብ የተሻለች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ በማስረከብ በኩልም ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ተናግረዋል። 


 

ኢትዮጵያ ከችግር፣ ከድህነት፣ ከመከፋፈል እና ከልመና ለማውጣት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሚናቸው ወሳኝ መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም