መንግስት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በላቀ ቁርጠኝነት እየሰራ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በላቀ ቁርጠኝነት እየሰራ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2017(ኢዜአ)፦ መንግስት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በላቀ ቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከመላው ኢትዮጵያ ከተውጣጡ መምህራን ጋር ውይይት አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በውይይቱ መንግስት በኢትዮጵያ ሰላምን ለማስፈን እያከናወናቸው ያሉ ስራዎችን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
መንግስት የሰላምን ጉዳይ በተቋም እንስራ በሚል የሰላም ሚኒስቴርን ማቋቋሙን አውስተው ከተቋሙ ባሻገር ከታጠቁ ኃይሎች ጋር ችግሮችን ለመፍታት ያላሰለሰ ጥረት ማድረጉን አመልክተዋል።
ይሁንና መንግስት ለሰላም ያቀረበውን ጥሪ እና የዘረጋውን እጅ ወደ ጎን በመተው ኃይልን እንደ አማራጭ እየተጠቀሙ ያሉ አካላት እንዳሉ ጠቅሰው ከውይይትና ከንግግር ውጪ ሌላ ሰላምን ማምጫ አማራጭ እንደሌለ ሊገነዘቡ ይገባል ብለዋል።
ጥሪውን ተቀብለው በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን የሰጡ ታጣቂዎችን ከመቀበል ባለፈ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በማድረግ ጭምር መንግስት ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በግልጽ ማሳየቱን አመልክተዋል።
ለኢትዮጵያ ሰላም ሲባል ችግሮችን በውይይት መፍታት ለሚፈልግ እና የተሻለ ሀሳብ አለኝ ላለ ማንኛውም አካል መንግስት ሁሌም በሩ ክፍት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
መንግስት የሰላም ጥሪን ወደ ጎን በመተው ሰውን ማገትና ትምህርት ቤት ማዘጋትን ጨምሮ የኃይል አማራጭን በወሰዱ ኃይሎች ላይ የሕግ ማስከበር እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አስታውቀዋል።
የፕሪቶሪያ ንግግር መንግስት ለሰላም ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነት በተግባር ያረጋገጠበት ነው ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ሰላም ያስፈጋታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ይህ እንዲሆን መንግስት በከፍተኛ ትጋት እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
ሰላም የሚሹ ኃይሎችን የሰላም ግንባታው ሂደት አካል በማድረግ በጋራ እንሰራለን ሲሉም ተናግረዋል።