የጋራ ትርክት ግንባታ ላይ መምህራን የበኩላቸውን ሚና መወጣት አለባቸው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የጋራ ትርክት ግንባታ ላይ መምህራን የበኩላቸውን ሚና መወጣት አለባቸው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2017(ኢዜአ)፦ የጋራ ትርክት ግንባታ ላይ መምህራን የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከመላው ኢትዮጵያ ከተውጣጡ መምህራን ጋር ውይይት አካሂደዋል።
በውይይታቸው ከመምህራኑ ለተነሱ በርካታ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት የጋራ ትርክት ለመገንባት ስትራተጂ እና ዕቅድ አዘጋጅቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ መምህራን ይህን መልካም ስራ በአግባቡ ተገንዝበው መደገፍ እንዳለባቸው አስረድተዋል።
የጋራ ትርክትን ስኬታማ ለማድረግ በትምህርት ቤቶች ሁልጊዜ ማስገንዘብ እንደሚገባ ገልጸው፤ ለዚህም መምህራን የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል።
መንግስት ያደሩ ችግሮችን በአምስት ማዕቀፎች ለመፍታት መወሰኑን አንስተው ችግሮችን በውይይትና በመደማመጥ እንፍታ በሚል በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በማቋቋም ወደ ተግባር መግባቱ አንዱና ዋነኛው መሆኑን ተናግረዋል።
ሁለተኛው ደግሞ የሽግግር ፍትህ በማቋቋም ያደሩ ችግሮችን በዘላቂነት በይቅርታና በፍትህ ለመፍታት የጀመረው ሥራ ስለመሆኑም አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሶስተኛውን ማዕቀፍ ሲያስረዱ ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን በማቋቋም የቀድሞ ታጣቂዎች ተሃድሶ ወስደው በሰላማዊ መንገድ ህይወታቸውን እንዲመሩ በማድረግ ረገድ ትልቅ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ስብራት ለማስተካከል ሀገር በቀል የብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግ ስኬቶችን ማስመዝገቡን ደግሞ በአራተኛ ማዕቀፍ ጠቅሰዋል።
ጠንካራ ተቋማት የመገንባትና የመንግት አገልግሎትን የማዘመን ሥራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑንም በአፅንኦት ገልጸዋል።