ቀጥታ፡

በሱዳን በተከሰተው ግጭት ምክንያት ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም በቅንጅት መስራት ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2017(ኢዜአ)፦ በሱዳን በተከሰተው ግጭት ምክንያት ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ዜጎችን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ፍትህ ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በሱዳን በተከሰተው ግጭት ተፈናቅለው ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ዜጎችን መልሶ ማቋቋም ላይ ትኩረት ያደረገ ምክክር እያካሄዱ ነው።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ሃላፊ አሳልፈው አህመዲን እንደገለጹት፤ ሚኒስቴሩ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ከመከላከል ጎን ለጎን ተመላሽ ዜጎች ማህበራዊ፣ ስነ ልቦናዊ እና ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ እንዲያገኙ እየሰራ ይገኛል፡፡

ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በተለይ ህጻናት፣ ሴቶችና አረጋውያን ሰብዓዊ ጉዳት እንዳይደርስባቸው በትኩረት እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

መድረኩ ተመላሽ ዜጎች ልዩ ልዩ ድጋፍ ስለሚያገኙበትና ከህብረተሰቡ ጋር ሊቀላቀሉ ስለሚችሉበት ሁኔታ የሚመክር መሆኑን አንስተው፤ በተለይም በተበታተነ መልኩ የሚሰጠው ድጋፍ ወደተደራጀና የተቀናጀ አግባብ ለማምጣት ግብዓት የሚገኝበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ለተመላሾች የሚደረገው ድጋፍ ኑሯቸውን በዘላቂነት የሚያቋቁም እንዲሆን ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

በፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊ ትብብር ጥምረት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አብርሃም አያሌው በበኩላቸው፤ ተመላሾቹ ሰብዓዊ መብታቸው እንዲጠበቅ ልዩ ልዩ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለተመላሾቹ ከሚደረገው ዕለታዊ ድጋፍ ባሻገር በዘላቂነት የሚቋቋሙበትን ስልት መቀየስ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

በተለያዩ ምክንያቶች ችግር ውስጥ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማገዝ የሁሉም ተቋም ሃላፊነት ነው ያሉት ደግሞ የዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት ተወካይ ሚሞሪ መዋሊ ናቸው፡፡

በመሆኑም ተመላሾቹን በዘላቂነት ለማቋቋም እጅ ለእጅ ተያይዞ መስራት እንደሚገባና በዚህ ረገድ የዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የምክክር መድረኩ ነገም ቀጥሎ እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም