የህብረት ስራ ማህበራት አሰራራቸውን በማዘመን ተወዳዳሪና ገበያ ተኮር እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ ነው - ኮሚሽኑ

ሆሳዕና፤ ሰኔ 6/2017(ኢዜአ)፦ የህብረት ስራ ማህበራት አሰራራቸውን በማዘመን ተወዳዳሪና ገበያ ተኮር እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን ገለፀ፡፡

"የህብረት ስራ ማህበራት ሚና ለዜጎች ሁለንተናዊ ብልፅግና!" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ 2ኛው ዙር የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሲምፖዝየም፣ ኤግዚቢሽንና ባዛር የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው በተገኙበት በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል፡፡

የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሺሰማ ገብረስላሴ በዚህ ወቅት እንዳሉት የህብረት ስራ ማህበራት ያላቸውን አቅም አሟጠው መጠቀም እንዲችሉ የአሰራር ማሻሻያ እያደረጉ ነው።

ህብረት ስራ ማህበራቱ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ከማስቻል አኳያ ያሉባቸውን ችግሮች የመለየት ስራ መሰራቱን ገልጸው በተለዩ ችግሮች ዙሪያ በተሰራው ሪፎርም በርካታ የህብረት ስራ ማህበራት ዳግም በማንሰራራት ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።

የህብረት ስራ ማህበራት አሰራርን በማዘመን ማህበራቱን ተወዳዳሪና ገበያ ተኮር ለማድረግ የተጀመረው ጥረት እንደሚጠናከርም ገልጸዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ኡስማን ስሩር፤ የህብረት ስራ ማህበራት በተለይ ግብርናን ከማዘመን አንጻር አበረታች ስራ እየሰሩ ነው።

በተጨማሪም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከማምጣት አኳያ ጉልህ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

በክልሉ የህብረት ስራ ማህበራትን በማጠናከር የማህበረሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራም ገልፀዋል፡፡

የክልሉ ህብረት ስራ ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ተመስገን ጎዴቦ በበኩላቸው በክልሉ የሚገኙ የህብረት ስራ ማህበራት ምርቶቻቸውን እንዲያስተዋውቁ እና ትስስር እንዲፈጥሩ ኤግዚቢሽንና ባዛሩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በክልሉ የህብረት ስራ ማህበራትን ለማጠናከር በተጀመሩ የሪፎርም ስራዎች ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የክልል፣ የዞንና የልዩ ወረዳ እና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮችና የህብረት ስራ ማህበራት አባላትና አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም