በክልሉ በግብርናው መስክ የተገኙ ውጤቶችን በማስቀጠል የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በግብርናው መስክ የተገኙ ውጤቶችን በማስቀጠል የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ

ሀዋሳ፤ ሰኔ 6/2017(ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል በግብርናው መስክ የተገኙ ውጤቶችን በማስቀጠል የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ የ2017/18 የምርት ዘመን የመኸር ወቅት የንቅናቄ መድረክ በሀዋሳ አካሂዷል።
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ እንደገለጹት የክልሉ መንግስት በግብርናው መስክ የተገኙ ውጤቶችን በማስቀጠል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ነው።
በዘርፉ ባለፉት አመታት የተገኙ ተሞክሮዎችን በመቀመርና ልማቱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማስደገፍ ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በዘንድሮ የመኽር ወቅትም እንደ ክልል የተያዙ እቅዶችን ለማሳካት የተጀመሩ ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የክልሉ መንግስት የቤተሰብ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ከቀረጻቸው ፓኬጆች 19ኙ በግብርናው ዘርፍ የሚተገበሩ በመሆናቸው አመራሩ በመቀናጀትና በሃላፊነት ሊመራው እንደሚገባ አሳስበዋል።
የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ሃላፊ መምሩ ሞኬ በበኩላቸው በዘንድሮው የመኸር ወቅት ከ159ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት እቅድ መያዙን ገልጸዋል።
በዚህም ከ20 ሚሊየን ኩንታል በላይ የዋና ዋናና የስራስር ሰብሎች ምርት እንደሚጠበቅ ገልጸው እቅዱ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 20 በመቶ ብልጫ አለው ብለዋል።
በምርት ዘመኑ ከተያዘው የመሬት ሽፋን ከፍተኛው በዋና ዋና ሰብሎች እንደሚሸፈን አመላክተዋል።
የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡ የስራስር ሰብሎችን የማስፋፋትና እንደ ክልል የቤተሰብ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በእርሻው ዘርፍ የተያዙ ፓኬጆችን ለማሳካት ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።
ለዚህም በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰው ለምርት ወቅቱ ለክልሉ ከተያዘው 300ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ እስካሁን 167ሺህ ኩንታሉ መግባቱን ገልጸዋል።
በቂ የምርጥ ዘር ዝግጅችና አሲዳማ አፈርን ማከም የሚያስችል 80ሺህ ኩንታል ኖራ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።
የዛሬው የንቅናቄ መድረክም በየደረጃው ያለው አመራር በእቅዱ ዙሪያ የጋራ መግባባት እንዲፈጥርና የተቀናጀ ድጋፍና ክትትል እንዲያደርግ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን አመልክተዋል።
በመድረኩ ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን በመኸር ልማት እቅዱና የትኩረት አቅጣጫዎች ባተኮሩ ሰነዶች ላይ ውይይት ተደርጓል።