ኢትዮጵያ ስደተኞችን በአካታችነት ተቀብላ ማስተናገዷን አጠናክራ ትቀጥላለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ስደተኞችን በአካታችነት ተቀብላ ማስተናገዷን አጠናክራ ትቀጥላለች
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ስደተኞችን በአካታችነት ተቀብላ ማስተናገዷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ተገለፀ።
የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ስደተኞችን በአካታችነት መደገፍን የተመለከተ ከፍተኛ የውይይት መድረክ እያካሔደ ነው።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ የረጅም ጊዜ ታሪክ አላት።
ስደተኞችን በአካታችነት በመቀበል የጤና፣ የትምህርትና ሌሎች አገልግሎቶችን በመስጠትና በምጣኔ ሃብት በዘላቂነት ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ በፖሊሲ ደረጃ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች እንደምትገኝ አስረድተዋል።
በተመሳሳይ መሰረታዊ በሆኑ አገልግሎቶች በወሳኝ ኩነት እንዲሁም ዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል።
በትምህርት ዘርፍ በመጀመሪያ ደረጃ፣ በቴክኒክና ሙያ እንዲሁም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ችላለች ብለዋል።
በምጣኔ ሃብት ዘርፍም በስራ እድል ፈጠራ በማካተት በዘላቂነት ራሳቸውን የሚችሉበት እድል የተፈጠረ ሲሆን፤ አብዛኞቹ ስደተኞች ይህን እድል እየተጠቀሙበት መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ስደተኞችን ታሳቢ ያደረገ የተቀናጀ እና አካታች አሰራሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስደተኞችን በአካታችነት በዘላቂነት ራሳቸውን እንዲችሉ እያከናወነች ላለው ተግባር ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሃሰን እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞችን ተቀብላ እያስተናገደች ትገኛለች።
መንግስት በዘላቂነት ስደተኞች ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ እየተገበራቸው ላሉ የተለያዩ መርሃ ግብሮች ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የቴክኒክና የገንዘብ ትብብሩን ሊያጠናክር ይገባል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ ራሚዝ አላክባሮቭ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ለስደተኞች ሁልጊዜም በሯን ክፍት በማድረግ የምትቀበል ሀገር ናት ሲሉ ገልጸዋል።
በመሆኑም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በጀቱን በማሳደግ መንግስት እያከናወነ ያለውን ተግባር ሊደግፍ ይገባል ብለዋል።
በውይይቱ የተባበሩት መንግስታት ተወካዮች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተገኝተዋል።