በኦሮሚያ ክልል በ400 ሺህ ሄክታር አዲስ መሬት ላይ የቡና ችግኝ ይተከላል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል በ400 ሺህ ሄክታር አዲስ መሬት ላይ የቡና ችግኝ ይተከላል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2017 (ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል በክረምቱ ወራት በ400 ሺህ ሄክታር አዲስ መሬት ላይ የቡና ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ የግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የቡናና ሻይ ዘርፍ ኃላፊ መሐመድ ሰኒ አሚን እንዳሉት በክልሉ የቡና ልማት በየጊዜው እየተስፋፋ ይገኛል።
በዚህም ለዘንድሮ ክረምት የቡና ምርጥ ዘር ችግኝ በብዛትና በጥራት ለመትከል የሚያስችል አስፈላጊ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል።
የቡና ችግኝ ተከላው በስፋት የሚካሄደው በክልሉ ቡና አብቃይ አካባቢዎች ሲሆን በኩታ ገጠም እንደሚለማና ተከላው በዋናነትም በ18 ዞኖች ውስጥ እንደሚከናወን ጠቅሰዋል።
በዚህም በክልሉ በ400 ሺህ ሄክታር ተጨማሪ አዲስ መሬት ላይ የቡና ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የችግኝ ተከላው እንደየአከባቢው ሁኔታ እንደሚካሄድ ገልጸው በሄክታር ከ2 ሺ 500 እስከ 3 ሺህ 300 በላይ ችግኝ የሚተከል መሆኑን አስረድተዋል።
አሁን ላይ አንዳንድ አካባቢዎች የቡና ችግኝ ተከላው እየተከናወነ መሆኑን እና አርሶ አደሩ በስፋት እየተሳተፈ እንደሚገኝ ጠቅሰው ድጋፍና ክትትልም እየተደረገላቸው ይገኛል ብለዋል።
በክልሉ ባለፉት 6 ዓመታት በሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የነበረው የቡና ሽፋን አሁን ላይ ወደ ሶስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መድረሱን ገልጸዋል።
በተመሳሳይም በክልሉ በ7 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሻይ ችግኝ ለመትከል የመሬት ልየታ እና ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የሻይ ልማቱም የሚካሄደው በጅማ፣ በኢሉአባቦር እና በቡኖ በደሌ ዞኖች ውስጥ መሆኑን ጠቅሰው ተከላው በኩታገጠም የሚከናወን እንደሆነም አስረድተዋል።
በሌላ በኩል በክረምቱ ወራት በርበሬ፣ ጥቁር አዝሙድ፣ ቆንዶ በርበሬ፣ የስጋ መጥበሻና ኮረሪማ የመሳሰሉ የቅመማ ቅመም ዓይነቶች በስፋት እንደሚከተሉ ተናግረዋል።
አርሶ አደሩ በተለይም ከበርበሬ፤ ከኮረሪማና ሌሎችም ተጠቃሚ እየሆነ ስለመጣ በልማት ስራው ላይ በከፍተኛ ፍላጎትና ተነሳሽነት እየተሳተፈ መሆኑንም ተናግረዋል።
በ2017/18 የምርት ዘመን የተለያዩ የቅመማ ቅመም ዓይነቶችን በ600ሺ ሄክታር መሬት ላይ ለማልማት ታቅዶ የመሬት ዝግጅት ስራው መጠናቀቁን አመልክተዋል።