ኢትዮጵያ ለስደተኞች የምታደርገውን ድጋፍ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲደግፍ በትኩረት እንሰራለን - ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ስደተኞችን በማስተናገድ እያከናወነች ያለውን መልካም ተግባር ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያውቅ እና ድጋፍ እንዲያደርግ በትኩረት እንሰራለን ሲሉ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ ገለጹ።

ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲን በብሄራዊ ቤተ መንግስት ተቀብለው በስደተኞች ዙሪያ አነጋግረዋል።

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲን ከውይይቱ በኋላ ዓለም አቀፍ ድጋፍ በተቀዛቀዘበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ስደተኞችን ማስተናገዷ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው፤ የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡




ኢትዮጵያ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የመጡ በርካታ ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ ላይ እንደምትገኝ የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ ይህንኑ መልካም ተግባር ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲደግፍ በትኩረት እንሰራለን ሲሉም ገልጸዋል።




ውይይቱን የተከታተሉት የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሀሰን እንደገለጹት፤ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ እና በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲን መካከል የተደረገው ውይይት ውጤታማ ነው።

በአሁኑ ወቅት ለስደተኞች የሚደረገው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድጋፍ እየቀነሰ መሆኑን ተከትሎ እገዛው በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ ትኩረት አድርገው መወያየታቸውን አንስተዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀስላሴ በቀጣናው ካለው የሰላም ጉዳይ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ አሁንም ስደተኞችን እየተቀበለች መሆኗን ማንሳታቸውን ጠቅሰው፤ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ለኮሚሽነሩ መግለጻቸውን አስታውቀዋል፡፡

ኮሚሽነሩ በቀጣይነት ድጋፉ እንደሚጠናከር ለፕሬዝዳንት ታዬ ቃል መግባታቸውን ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡

ኢትየጵያ ስደተኞችን ተቀብላ ማስተናገዷን አድንቀው ለዚህ ተግባሯ ኮሚሽነሩ ትልቅ እውቅና መስጠታቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።

ኢትየጵያ ዓለም አቀፍ ህጎችን በማክበር ስደተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ህጎችና አሰራሮችን በማውጣት ለዓለም ምሳሌ መሆን የሚችል ስራ እየሰራች ትገኛለች፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም