የድሬዳዋን ልማትና ኢንቨስትመንት ለማጠናከር ያለመ የዳያስፖራ ሳምንት ሊካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የድሬዳዋን ልማትና ኢንቨስትመንት ለማጠናከር ያለመ የዳያስፖራ ሳምንት ሊካሄድ ነው

ድሬዳዋ፤ ሰኔ 6/2017(ኢዜአ)፦ የድሬዳዋን ልማትና ኢንቨስትመንት ለማጠናከር ያለመ የዳያስፖራ ሳምንት ሊካሄድ መሆኑን የአስተዳደሩ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ገለጸ።
የከንቲባው ፅህፈት ቤት እና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ ገበየሁ ጥላሁን በሰጡት መግለጫ፤ በመላው አለም የሚገኙ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች የሚሳተፉበት አራተኛው አለም አቀፍ ሳምንት ለማክበር ዝግጅት ተጠናቋል።
ከመጪው ሐምሌ 21/2017 ጀምሮ ለአንድ ሳምንት "ድሬ ናፍቆት ለድሬ ብልፅግና" በሚል መሪ ሀሳብ በሚከበረው በአል ላይ ከመላው አለም የሚመጡ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች በለውጥ ጉዞ ላይ ይመክራሉ ብለዋል።
ባለፉት ሶስት አመታት የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች የህዝቡን ማህበራዊ ችግሮች ከማቃለል፤ የወል ትርክትን በመገንባት ረገድ ጉልህ ድርሻ ማበርከታቸውን አንስተዋል።
የዘንድሮውም ጅምር ስራዎችን በማጠናከር የድሬዳዋን የብልጽግና ጉዞ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሻገር የድርሻቸውን የሚወጡበት ነው ብለዋል።
በድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ፅህፈት ቤት የዳያስፖራ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ዳይሬክተር ቢንያም ግርማ በበኩላቸው ቀደም ሲል የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የኩላሊት ዕጥበት ህክምና ማዕከል መገንባታቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የትምህርት ቤት ምገባ እና የማዕድ ማጋራት ላይ መሳተፋቸውን አስረድተዋል።
በኢንቨስትመንት ዘርፉም በስራ ዕድል ፈጠራና የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።
ወደ ድሬዳዋ የሚመጡ ዳያስፖራዎችና ወዳጆች ከአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በሀገራቸው የለውጥ ጉዞ ላይ እንደሚመክሩም ይጠበቃል ብለዋል።
በተጨማሪም በኢንቨስትመንት አማራጮች፣ የቱሪዝም ሃብቶች ልማት ላይ እንደሚመክሩም ጠቁመዋል።
እንዲሁም አስተዳደሩ ለዳያስፖራው ማህበረሰብ ባዘጋጀው መሬት ላይ የመኖሪያ ቤት ግንባታ እንደሚጀምሩም ገልጸዋል።