በበጀት ዓመቱ ለ315 ዜጎች የተሳካ የዐይን ብሌን ንቅለ ተከላ ህክምና ተከናውኗል - ኢዜአ አማርኛ
በበጀት ዓመቱ ለ315 ዜጎች የተሳካ የዐይን ብሌን ንቅለ ተከላ ህክምና ተከናውኗል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ለ315 ዜጎች የዐይን ብሌን ንቅለ ተከላ ህክምና በተሳካ ሁኔታ በበጀት ዓመቱ መስጠት መቻሉን የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት አስታወቀ።
በማህበረሰቡ ዘንድ እየዳበረ የመጣውን የደም እና የዐይን ብሌን ልገሳ ተግባር ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ አገራዊ ንቅናቄ ሰኔ 7/2017 ዓ.ም እንዲሚካሔድ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃብታሙ ታዬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የዐይን ብሌን ንቅለ ተከላ ህክምና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
ቀደም ሲል የዐይን ብሌን ንቅለ ተከላ ህክምና በተለያየ መልኩ ይሰጥ እንደነበረ አስታውሰው፤ ይህ ሁኔታ ህክምናው ወጥነት ባለው መልኩ ተደራሽ እንዳይሆን አድርጎት መቆየቱን ተናግረዋል።
በመሆኑም የህክምና አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ እንዲያግዝ ታልሞ ህክምናው በኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ስር እንዲሰጥ መደረጉንም ገልጸዋል።
ይህም የህክምና አገልግሎቱ ፍትሃዊና ተደራሽ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ዓይነተኛ ሚና ማበርከቱንም ጠቁመዋል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ 315 ለሚሆኑ ዜጎች የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ ህክምና መሰጠቱን ጠቁመው፤ በዚሁ ዓመት እንዲሁ 522 ሰዎች የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል ገብተዋል ብለዋል።
ህክምናው በስፋት እየተሰጠ የሚገኘው በአዲስ አበባ ዳግማዊ ምኒልክ ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሲሆን ህክምናውን በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች ተደራሽ የማድረግ ስራ ትኩረት ተሰጥቶታል ሲሉም ገልጸዋል።
ለአብነትም በሃዋሳ፣ በጎንደር፣ በጅማና መቀሌ ሆስፒታሎች ላይ የዓይን ብሌን ቀዶ ህክምናው እየተሰጠ መሆኑን አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት የዐይን ብሌን የማንሳት ስራ በሚኒሊክ ሆስፒታል ብቻ የሚሰራ ሲሆን ብሌኑን በመሰብሰብ ለህክምና ተቋማቱ ተደራሽ የሚያደርገው የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት መሆኑንም ጠቁመዋል።
ይህም የተደራሽነት ጥያቄን ያስከተለ በመሆኑ የዓይን ብሌንን የሚሰበስቡ ተቋማትን ለማስፋት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
በዚህ ረገድ በተከናወኑ ተግባራት ጅማ ከተማ ላይ የዓይን ባንክ ተቋምን የማቋቋም ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም ባለሙያዎችን መመደብና ማሰልጠን ጨምሮ አገልግሎቱን ለመጀመር የሚያስችል ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይ በጀት ዓመት እንደ አገር ተጨማሪ የዓይን ባንክ እንደሚኖር ይጠበቃል ብለዋል።
በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት በማህበረሰቡ ዘንድ ደም የመለገስ ተግባር እየዳበረና ባህል እየሆነ መምጣቱን ዋና ዳይሬክተሩ አክለዋል።
በአለም አቀፍ ደረጃ በሰኔ ወር የሚከበረውን የዓይን ብሌንና የደም ልገሳ ቀን ምክንያት በማድረግ በኢትዮጵያ ሰኔ 7/2017 አገራዊ ንቅናቄ እንደሚካሔድ ገልጸዋል።
“የህይወትና የብርሃን ስጦታ ያበርክቱ ደም ይለግሱ የዐይን ብሌን ይለግሱ” በሚል መሪ ሀሳብ የሚከበረውን ይህን ዓለም አቀፍ በዓል በተለያዩ መረሃ-ግብሮች ለማክበር ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል።
በእለቱ በደም ልገሳና በዓይን ብሌን ልገሳ ዙሪያ የማህበረሰብ ንቅናቄ መፍጠር፣ የዓይን ብሌን እንዲሁም በተከታታይ ደም የለገሱ ዜጎች እውቅና የመስጠትና ተግባሩ አመቱን ሙሉ እንዲከወን የማድረግ ስራ ትኩረት እንደሚሰጠው ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የዐይን ብሌን ንቅለ ተከላ ህክምና የተጀመረው በ1995 ዓ.ም ሲሆን እስከ አሁን ለ3ሺህ500 ዜጎች ህክምናው መሰጠቱን ከኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።