የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ለመስጠት የሚያስፈልገውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቀናል-ዩኒቨርሲቲዎች

አዲስ አበባ፤ሰኔ 6/2017 (ኢዜአ)፦የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ለመስጠት የሚያስችላቸውን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ማጠናቀቃቸው ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ገለጹ፡፡

የ2017 ዓም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከሰኔ 23 እስከ ሀምሌ 8 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ እንደሚሰጥ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።

በመላ ሀገሪቱም ከ600 ሺህ በላይ የተፈጥሮ እና የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ፈተናውን በወረቀት እና በበይነ መረብ እንደሚወስዱ የወጣው ፕሮግራም ያሳያል።

ኢዜአ ፈተናው ከሚሰጥባቸው መካከል የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እና የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲን አነጋግሯል፡፡

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ደረጀ እንግዳ የዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በወረቀትና በቴክኖሎጂ በተደገፈ መልኩ እንደሚሰጥና ለዚህ የሚረዳ በቂ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል። 

በዩኒቨርሲቲው ከ10 ሺህ በላይ የማህበራዊና የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ፈተናቸውን እንደሚወስዱ ጠቅሰው ከነዚህ መካከል ከስድስት ሺህ በላይ ተማሪዎች ፈተናውን በበይነ መረብ እንደሚፈተኑ ተናግረዋል።

በዚህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ዩኒቨርሲቲው በበይነ መረብ የሚፈትናቸውን ተማሪዎች ቁጥር በእጥፍ ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።

ተማሪዎች ለፈተና ሲመጡ የፋይዳ መታወቂያ መያዝ ግዴታ መሆኑን በመገንዘብ መታወቂያቸውን ይዘው እንዲመጡ አሳስበዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ለማ ጉዲሳ በበኩላቸው በሀገር አቀፍ ፈተናው 7 ሺህ 916 የተፈጥሮ እና የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው እንደሚፈተኑ ተናግረዋል።

ዶክተር ለማ አክለውም ከዚህ ቀደም በፈተና አሰጣጡ ላይ ሲያጋጥሙ የነበሩ ተግዳሮቶች እንዳይደገሙ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን ጠቅሰዋል።

ዶክተር ደረጀ ሀገር አቀፍ ፈተናው ተማሪዎች በእውቀት ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ ራሳቸውን የሚፈትሹበት በመሆኑ ያለምንም መጨናነቅ ራሳቸውን በስነ ልቦና በማዘጋጀት ፈተናውን እንዲወስዱ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በተለይም በኦንላይን የሚፈተኑ ተማሪዎች ራሳቸውን ለፈተናው ዝግጁ ከማድረግ ባለፈ ከቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ የሚያሳስባቸው ነገር ሊኖር እንደማይገባ አስገንዝበዋል።

ዩኒቨርሲቲዎቹ ቀደም ብለው ለፈተናው አጋዥ የሆኑ የመኝታ፣ የጥናት የመመገቢያና እና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶችን ማመቻቸታቸውን አስታውቀዋል።

በቀጣዮቹ ዓመታት ፈተናውን ሙሉ በሙሉ በበይነ መረብ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑንም ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያሳያል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም