የኢትዮጵያን በጎ ገጽታ በዓለም አቀፋዊና ቀጣናዊ መድረኮች ለማስተዋወቅ የዜጎችን ንቁ ተሳትፎ ይጠይቃል - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን በጎ ገጽታ በዓለም አቀፋዊና ቀጣናዊ መድረኮች ለማስተዋወቅ የዜጎችን ንቁ ተሳትፎ ይጠይቃል - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን በጎ ገጽታ በዓለም አቀፋዊና ቀጣናዊ መድረኮች ለማስተዋወቅ ከመደበኛው የመንግሥት ሥራ በተጨማሪ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ዜጎች በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሀደራ አበራ ገለጹ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የውጭ ጉዳይ ኢኒስቲትዩት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር በመተባበር ለወዳጅነት ቡድኖችና ፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባላት ያዘጋጁት ስልጠና ተጀምሯል።
ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት በሚቆየው ስልጠና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፣ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ፣ የጎረቤት ሀገራትና የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ እንዲሁም ሌሎች የውጭ ግንኙነት ስልቶች ይዳሰሳሉ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሀደራ አበራ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ሀገራዊ ልማትና ብልጽግናን እውን ለማድረግ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ተለዋዋጭና ኢ-ተገማች በሆነው የዓለም ነባራዊ ሁኔታ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ዘርፈ ብዙ እና የተደራጀ የዲፕሎማሲ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።
ለዚህ ደግሞ የዓለም ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስርዓቱ የሚጠይቀውን የውጭ ግንኙነት ስልት መንደፍና መከተል አስፈላጊ መሆኑን አመልክተው፤ የዓለም አስቻይ ሁኔታዎችን በጥንቃቄ በማየት በአስተውሎት መራመድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በዚህም የውጭ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ አጋርነትን ለማጠናከር፣ ገጽታ ለመገንባት፣ የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ሁሉም አካላት በጋራ መረባረብ አለባቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች እንደምትገኝ ገልጸው፤ የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብሩ ስትራቴጂያዊ አጋሮችን የማብዛት ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።
በመርህ ላይ የተመሰረተ ዓለም አቀፋዊ እና ቀጣናዊ አጋርነትን ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ በባለብዙ ወገን መድረኮች የሚተላለፉ ውሳኔዎች የኢትዮጵያን ተደማጭነትና ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቁ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ፣ የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት፣ የአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት፣ እንዲሁም የብዝሀ ብሔር መገኛ መሆኗን በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራችን መግለጽና ገጽታዋን መገንባት አለብን ሲሉም አስገንዝበዋል።
ለዚህ ደግሞ መንግስት ከሚሰራው የውጭ ግንኙነት ስራዎች ባሻገር በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሽብሩ ማሞ በበኩላቸው፤ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ የሀገራችን መልካም ገጽታ መገንባት፣ አጋርነትና ወዳጅነትን ማብዛት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ፐብሊክ ዲፕሎማሲ በመንግሥታት ግንኙነት ብቻ የታጠረውን የሀገራት ግንኙነት በህዝቦች መካከል እንዲዳብር ያስቻለ ነው ብለዋል፡፡
በተለይም የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የምርምር ተቋማትና የተለያዩ የሙያ ማህበራት የሀገርን ገጽታ በማስተዋወቅ በኩል ሚናቸው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡