የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች እጩዎች ይፋ ሆኑ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች እጩዎች ይፋ ሆኑ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር የ2017 የሊጉን ኮከብ ተጫዋች እጩዎች ዝርዝር ዛሬ ይፋ አድርጓል።
ተመልካቾች ለተጫዋቾች ድምጽ መስጠት የሚችሉበት አማራጭ ማዘጋጀቱንም ገልጿል።
ማህበሩ ለኮከብ ተጫዋችነት እጩ የሆኑ ሰባት ተጫዋቾችን አሳውቋል።
ከሻምፒዮኑ ኢትዮጵያ መድን ሀይደር ሸረፋ፣ መሐመድ አበራ እና ዳዊት ተፈራ ፣ ራምኬል ጀምስ እና ዲቫይን ዋቹኩዋ ከኢትዮጵያ ቡና፣ የሃዋሳ ከተማው ዓሊ ሱሌይማን እና የመቻሉ ሽመልስ በቀለ በእጩነት ቀርበዋል።
በኮከብ ወጣት ተስፈኛ ተጨዋች ዘርፍ በረከት ካሌብ ከኢትዮጵያ መድን፣ ይታገሱ ታሪኩ ከኢትዮጵያ ቡና፣ ሄኖክ ዮሐንስ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ሄኖክ ይበልጣል ከባህር ዳር ከተማ እና ዘረሰናይ ብርሃነ ከመቀሌ 70 እንደርታ እጩዎች ዝርዝር ውስጥ ተካትዋል።
አቡበከር ኑራ ከኢትዮጵያ መድን፣ ዳንላንድ ኢብራሂም ከኢትዮጵያ ቡና እና ፔፔ ሰዒዶ ከባህር ዳር ከተማ የኮከብ ግብ ጠባቂ እጩዎች ናቸው።
ተመልካቾች በተለያየ ዘርፍ የቀረቡትን ተጫዋቾች እስከ ሰኔ 13 ቀን 2017 ዓ.ም መምረጥ እና በ https://t.me/ethiopianlea የአክሲዮን ማህበሩ የቴሌግራም ገጽ ድምጽ መስጠት እንደሚችሉ ገልጿል።
ከተመልካቾች ድምጽ በተጨማሪ አሰልጣኞች፣ ጋዜጠኞችና የሊጉን ጨዋታ የቀጥታ ስርጭት መብት የወሰደው የደቡብ አፍሪካው ሱፐር ስፖርት የቴሌቪዥን ጣቢያ በድምጽ አሰጣጡ ድርሻ እንዳላቸው ማህበሩ ገልጿል።
በ2016 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ ጋናዊው ባሲሩ ዑመር ኮከብ ተጫዋች፣ ቢኒያም አይተን ኮከብ ተስፈኛ ተጫዋች እና ፍሬው ጌታሁን ኮከብ ግብ ጠባቂ ተብለው መመረጣቸው የሚታወስ ነው።