በክልሉ የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ በሚደረገው ጥረት የታማኝ ግብር ከፋዮች ድርሻ ጉልህ ነው - ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ

ሀዋሳ፤ ሰኔ 6/2017(ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ በሚደረገው ጥረት የታማኝ ግብር ከፋዮች ድርሻ ጉልህ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

በክልሉ "ታማኝ ግብር ከፋይ ብርቱ የልማት አርበኛ ነው" በሚል መሪ ሃሳብ ለግንባር ቀደም ግብር ከፋዮች የተዘጋጀ የእውቅናና ሽልማት መርሃ ግብር ተካሂዷል።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንደተናገሩት በክልሉ የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ በሚደረገው ጥረት የታማኝ ግብር ከፋዮች ሚና ጉልህ ነው።

ባለፉት አምስት ዓመታት በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መሰረተ ልማቶች ክልሉ በሚያመነጨው ገቢ የሚሰሩ በርካታ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም ግብር ከፋዩ በክልሉ ልማትና እድገት ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ እንዲያጠናክርም አሳስበዋል።

የክልሉ መንግስትም ለህዝቡና ለግብር ከፋዩ የተቀላጠፈ አገልግሎት በመስጠት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቅሰው የንግዱ ማህበረሰብ የሚያጋጥመውን ተግዳሮት የሚቀርፍ አሰራር መዘርጋቱን ተናግረዋል።

የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ደምሴ እሳቱ በበኩላቸው የክልሉን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ የገቢ አቅምን የማሳደግና ገቢን በአግባቡ የመሰብሰብ ስራ በትኩረት እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም 15 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው በ11 ወራት ውስጥ ከ12 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

በቀሪ ወራትም የተያዘውን እቅድ በማሳካት በክልሉ ልማትና እድገት ላይ ጉልህ ሚና ለመጫወት በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

እውቅናና ሽልማት የተሰጣቸው ታማኝ ግብር ከፋዮችም በ2016 በጀት ዓመት የሚጠበቅባቸውን ግብር በመክፈል የዜግነት ግዴታቸውን የተወጡ የሀገር ባለውለታ መሆናቸውን ገልጸዋል።

እውቅናና ሽልማት ከተሰጣቸው ግብር ከፋዮች መካከል አቶ አብርሃም ኮባቶ ግብር መክፈል ለሀገር ልማትና የሚፈለገውን ብልጽግና ለማረጋገጥ የማይናቅ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።

የተሰጣቸው እውቅናም የበለጠ እንዲሰሩ ከፍተኛ አቅም እንደሚሰጣቸው በመግለጽ።

ድርጅታቸው በተቋቋመ በአንድ ዓመት ውስጥ የሚጠበቅበትን ግብር በመክፈሉ እውቅና ማግኘቱን የገለጹት ደግሞ የሲዳማ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ኤሊያስ ቲሮ ናቸው።

በቀጣይ የበለጠ በመስራት በሀገር ልማትና እድገት ላይ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።

ዛሬ እውቅናና ሽልማት የተሰጣቸው ግብር ከፋዮች ሁለት የልማት ድርጅቶችን ጨምሮ በቁጥር 55 ሲሆኑ ከ2 እስከ 57 ሚሊዮን ብር በላይ ግብርን በታማኝነት የከፈሉ መሆናቸውም ታውቋል።

ለታማኝ ግብር ከፋዮቹም የሰርተፊኬት፣ የሜዳሊያና የዋንጫ እንዲሁም የተለያየ ሽልማትና እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም