አክሲዮን ማህበሩ ባቡር በሚያልፍባቸው አካባቢዎች ስድስት ትምህርት ቤቶች ሊገነባ ነው

ድሬደዋ፣ ሰኔ 6/2017(ኢዜአ)፡-የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር አክሲዮን ማህበር ባቡር በሚያቋርጣቸው አካባቢዎች ስድስት ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ዝግጅት ማጠናቀቁን ገለጸ።

አክሲዮን ማህበሩ የባቡር ሰላምና ደህንነትን በተቀናጀ መንገድ ለመጠበቅ ባቡሩ በሚያልፍባቸው አካባቢዎች ከሚገኙ  የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር  በቅርበት እየሰራ መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር  አክሲዮን ማህበር የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ ሙና አህመድ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ባቡሩ በሚያልፍባቸው ክልሎችና ከተሞች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የባቡሩን ደህንነት በመጠበቅ ኃላፊነታቸውን  እየተወጡ ነው።

እነዚህን ተግባራት ይበልጥ ለማሳደግ አክሲዮን ማህበሩ ባቡሩ በሚያልፍባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ማህበራዊ ኃላፊነቱን ይወጣል ብለዋል።

አክሲዮን ማህበሩ ከማህበረሰቡ ጋር ተቀናጅቶ በመስራቱ የማህበረሰቡ የባለቤትነት መንፈስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱንም ተናግረዋል።

በዚህም አክሲዮን ማህበሩ ስድስት ዘመናዊ ሁለተኛ ደረጃ  ትምህርት ቤቶችን  ገንብቶ ለማህበረሰቡ ያስረክባል ብለዋል።

በአክሲዮን ማህበሩ የሚኤሶ-ደወሌ የማህበረሰብ እና ባለድርሻ አካላት ቡድን መሪ ምክትል ኮማንደር ጉልማ ታዬ፤ የባቡር ደህንነትን በአስተማማኝ መንገድ መጠበቅ እንደሚገባ ጠቅሰው ባህላዊ መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች ድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ይህንን ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው በተለይ ባቡሩ በሚጓዝበት መስመሮች የሚኖሩ ወጣቶች የስራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተለይ አክሲዮን ማህበሩ በሚቀጥለው ዓመት ስድስት ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት መዘጋጀቱ በጎ እንቅስቃሴ መሆኑንም አመልክተዋል።


 

''ህብረተሰቡን በማስተባበር የባቡር ደህንነትን እየጠበቅን እንገኛለን'' ያሉት ደግሞ የሶማሌ ኢሳ ማህበረሰብ ባህላዊ መሪና የዑጋዝ ተወካይ አቶ አብዶ ዑመር ናቸው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም