በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደረሱ ጥቃቶችን ለመከላከል ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር ይገባል - ሚኒስቴሩ

ቦንጋ፤ ሰኔ 6/2017(ኢዜአ)፦ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደረሱ ጥቃቶችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛን ለመከላከልና ለማስቆም ያለመ የአመራር ንቅናቄ መድረክ በቦንጋ ከተማ አካሂዷል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂክማ ኬይረዲን፤ የባለድርሻ አካላትን ቅንጅት ማጠናከር በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደረሱ ጥቃቶችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል መሰረት መሆኑን ገልፀዋል።

በተለይ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛና ጥቃቶች ተፈፅመው ሲገኙ ተጠያቂነትን በማስፈን ረገድ የፍትሕ አካላት ሚና የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

በመድረኩ የተገኙት በብልፅግና ፓርቲ የሴቶች ክንፍ አደረጃጀት ዘርፍ ሀላፊ አሰለፈች ታደስ፣ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል የሀይማኖት አባቶችና ሌሎች ተሰሚነት ያላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ይበልጥ መስራት ይገባቸዋል ብለዋል።

ከዚህ በተጓዳኝ የሴቶች አደረጃጀቶችን በማጠናከር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን በማሳደግ ተጋላጭነታቸውን መቀነስ እንደሚገባም ገልጸዋል።


 

ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር በሴቶችና ሕፃናት ላይ ይደርሱ የነበሩ ጥቃቶችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እየቀነሱ መምጣታቸውን የተናገሩት ደግሞ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ ገነት መኩሪያ ናቸው።

በክልሉ ሁሉም ቀበሌዎች የጎጂ ልማዳዊ ድርጊት አስወጋጅ ግብረ ሀይል በማቋቋም በተሰራው ስራ 121 ቀበሌዎችን ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ነፃ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።

ለውጤቱም የባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም ይህን ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከርና የንቅናቄ ስራዎችን እስከታች ማውረድና መከታተል ላይ ትኩረት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።


 

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰብስቤ ሻዎኖ፤ የሴቶችንና ሕፃናትን መብትና ደሕንነት ማስጠበቅ ቅድሚያ የሚጠው ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

ችግሩን ለመከላከል በተደረገው ጥረት የታዩ መሻሻሎችን ለማስቀጠል ተጠያቂነትን የማስፈን ስራ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።


 

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቆጭቶ ገብረማሪያም በበኩላቸው የሴቶችና ሕፃናትን መብት ለማስጠበቅ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም