በክልሉ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የአልጋ አጎበር ስርጭት እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የአልጋ አጎበር ስርጭት እየተከናወነ ነው

ጂንካ፤ ሰኔ 6/2017(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የወቅቱን ዝናብ ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የወባ በሽታ ለመከላከል ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የአልጋ አጎበር ስርጭት እየተከናወነ ይገኛል።
የክልሉ ጤና ቢሮ በአሪ ዞን ባይፅማል ቀበሌ የአልጋ አጎበር ስርጭት አስጀምሯል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ መና መኩሪያ በወቅቱ እንደገለፁት በክልሉ የወባ በሽታ በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ህብረተሰቡን ያሳተፈ የበሽታ መከላከል ስራ እየተከናወነ ነው።
ዛሬ የተጀመረው የአልጋ አጎበር ስርጭት በክልሉ የወባ ተጋላጭ በሆኑ 22 ወረዳዎች ስር ለሚገኙ 325 ቀበሌዎች ተደራሽ እንደሚሆን አመላክተዋል።
በመርሃ ግብሩ ከ810ሺህ በላይ የአልጋ አጎበሮች እንደሚሰራጩ ጠቅሰው፥ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አመላክተዋል።
በስርጭቱ ህፃናት፣ ነፍሰ-ጡርና የሚያጠቡ እናቶች እንዲሁም አዛውንቶች ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው አቶ መና ተናግረዋል።
የአልጋ አጎበርን በአግባቡ በመጠቀም ከወባ በሽታ ራስን መከላከል ይገባል ያሉት ደግሞ የክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አጉኔ አሾሌ ናቸው።
የወባ መከላከል ስራውን ውጤታማ ለማድረግ የአካባቢ ቁጥጥር ስራው ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
ህብረተሰቡ የወባ በሽታ ምልክቶች ሲመለከት በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ምርመራ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአሪ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ ይሁን ጋሎ በበኩላቸው ዞኑ ለወባ ተጋላጭ ከሆኑ አካባቢዎች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።
በዞኑ የህብረተሰቡን የወባ ተጋላጭነት ለመቀነስ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የወባ መከላከል ስራዎች በትኩረት እየተሰሩ መሆኑን አንስተዋል።
ወቅቱ ለወባ ትንኝ መራቢያነት ምቹ በመሆኑ የአካባቢ ቁጥጥር ስራው ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል።
የአጎበር ስርጭቱ በዞኑ የሚከናወኑ የወባ መከላከል ስራዎችን እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።
የአልጋ አጎበር ድጋፍ ከተደረገላቸው የባይፅማል ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል አርሶ አደር ብዙነሽ ባህሩ፤ በአካባቢያቸው ለወባ ትንኝ መራቢያነት አመቺ የሆኑ ስፍራዎችን በማፅዳት፣ ያቆሩ ቦታዎችን በማፋሰስና በማዳፈን የወባ መከላከል ስራው ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ሌላው የቀበሌው ነዋሪ አርሶ አደር ዘውዴ ሺቺ በበኩላቸው በአካባቢው ለወባ ትንኝ መራቢያነት አመቺ የሆኑ ቦታውችን በመለየት ጽዳት እያካሄዱ መሆናቸውን ተናግርዋል።
የአልጋ አጎበር ስርጭቱ በክልሉ በሚገኙ 325 ቀበሌዎች እስከ ቀጣይ ሳምንት ተደራሽ እንደሚሆን ቢሮው አስታውቋል።
ከአልጋ አጎበር ስርጭቱ ጎን ለጎን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችም ትኩረት የተስጣቸው ናቸው።