እየተካሔዱ ያሉ የህዝብ ውይይቶች ዜጎች ለብሔራዊ ጥቅም መከበር የበኩላቸውን እንዲወጡ የሚያግዙ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
እየተካሔዱ ያሉ የህዝብ ውይይቶች ዜጎች ለብሔራዊ ጥቅም መከበር የበኩላቸውን እንዲወጡ የሚያግዙ ናቸው

ሚዛን አማን፤ ሰኔ 6/2017(ኢዜአ)፦እየተካሔዱ ያሉ የሕዝብ ውይይቶች ዜጎች ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታን በአግባቡ በመረዳት ለብሔራዊ ጥቅም መከበር የበኩላቸውን እንዲወጡ እንደሚያግዙ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
መንግስት በዞን፣ በክልልና በከተሞች ደረጃ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ተከታታይ ውይይት እያደረገ ይገኛል።
ሰሞኑንም ይኽው ውይይት ቀጥሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) ከተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ከተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት እያደረጉ ነው።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንም መንግስት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከዜጎች ጋር እያደረገ ያለው ውይይት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መጠናከር ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ልማት ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር ዋሲሁን በዛብህ እንዳሉት ዜጎች ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታን በአግባቡ በመረዳት ለብሔራዊ ጥቅም መከበር የበኩላቸውን እንዲወጡ ተከታታይ ውይይቶች አስፈላጊ ናቸው።
ከዚህም ባለፈ እየተደረጉ ያሉ ተከታታይ ውይይቶች የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ለዜጎች ለማስገንዘብና አገራዊ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ የጋራ ርብርብ እንዲደረግ ያግዛል ብለዋል።
የሀገር ግንባታ የሁሉንም የነቃ ተሳትፎ ይጠይቃል ያሉት መምህር ዋሲሁን ለተግባራዊነቱም መሰል ውይይቶች በሀገራዊ ጉዳይ የጋራ አረዳድ በመያዝ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲዳብር እንደሚያግዝ አመልክተዋል።
በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ቢመርቅ በሪሁን በበኩላቸው እየተካሄዱ ያሉ ውይይቶች ልማትን ለማፋጠንና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን ለማጠናከር ያግዛሉ ብለዋል።
መንግሥትም ከዜጎች የሚነሱ ጥያቄዎችን በቅርበት ተረድቶ እንደ አስፈላጊነቱ ምላሽ እንዲሰጣቸው ትልቅ እድል ይፈጥራል ሲሉም ገልጸዋል።
በተጨማሪም ውይይቶቹ መንግስት ብሔራዊ ጥቅሞችን ለማስከበር የሚያደርገውን ጥረት ለማሳካት ማኅበረሰቡ ነባራዊ ሁኔታዎችን ተገንዝቦ የበኩሉን ድርሻ እንዲያጠናክር የሚያደርግ እንደሆነም አመልክተዋል።
በመንግሥትና ሕዝብ መካከል ግልጸኝነትን ለመፍጠር የሚደረጉ መሰል የውይይቶች ለዴሞክራሲ ግንባታ ትልቅ ትርጉም አላቸው ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር አለማየሁ አብርሃም ናቸው።
በተለይም መንግስት ከምሁራን ጋር የሚያደርገውን ውይይት በማጠናከር ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ሀሳቦችን የሚያገኝበት መሆኑንም ተናግረዋል።