ቀጥታ፡

ከዋናው የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ርቀው የሚገኙ ዜጎችን የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች ውጤታማ ናቸው -የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ሰኔ 6/2017 (ኢዜአ)፦ከዋናው የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ርቀው የሚገኙ ዜጎችን የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጸ፡፡

የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፥ ባለፉት ዓመታት ከዋናው የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር የራቁ የህብረተሰብ ክፍሎችን የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ አማራጭ ኃይልን የማቅረብ ስራዎች በስፋት ተከናውነዋል።

የሶላር ኢነርጂን በማስፋፋት በርካታ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቁመው፥በዚህም የጤና ተቋማትን እና ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ሎሌች የማህበረሰቡ መገልገያዎችን የሃይል ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

እስከ ባለፈው ዓመት ድረስም ከ10 ሺህ በላይ ደንበኞች የሶላር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው፤ ከዋናው መስመር የራቁ ቦታዎች ላይ አማራጭ ኃይል የማቅረብ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል፡፡

በሚኒስቴሩ የገጠር ኢነርጂ ቴክኖሎጂ ልማትና ሽግግር ሥራ አስፈጻሚ ብርሃኑ ወልዱ በበኩላቸው፥ሚኒስቴሩ ከዋናው የኃይል መስመር ርቀው ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የሶላር ኢነርጂ በማስፋፋት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

እስካሁንም 18 የገጠር ከተሞች ላይ ማስፋፋት ማቻሉን ጠቁመው፤ በዚህም ነዋሪዎችን የመብራት ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር ለትናንሽ ቴክኖሎጂዎች ማለትም ለብረታ ብረትና ለእንጨት ውጤቶች ስራ፣ ለወፍጮ ቤቶችና ለሌሎች አገልግሎቶች ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም ከዋናው የኃይል መስመር ርቀው የሚገኙ ተቋማትን ኃይል እንዲያገኙ ከማድረግ አንጻር በጤና ተቋማትና ትምህርት ቤቶች ተደራሽ የማድረግ ስራ እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስቴሩ በዚህም የገጠሩን ማህበረሰብ የዘመናዊ የሃይል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የማድረግ ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም