ኢትዮጵያ ሰውሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን በመቋቋም የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ውጤታማ ሥራ አከናውናለች

አዲስ አበባ፤ሰኔ 6/2017 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ሰውሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎችን በመቋቋም የ2030 ዘላቂ የልማት ግቦችን የሚያሳኩ ውጤታማ ተግባራትን ማከናወኗን የ3ኛው ሀገር አቀፍ የዘላቂ ልማት ግቦች የፈቃደኝነት ግምገማ ሪፖርት አዘጋጅና የኢኮኖሚ አማካሪው ዳዊት አየለ ገለጹ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያጸደቀው የ2030 ዘላቂ የልማት አጀንዳ 17 ግቦችን ያካተተ ሲሆን፥ ከ2016 ጀምሮ ኢትዮጵያን ጨምሮ አባል ሀገራት በፈቃደኝነት ግቦችን ለማሳካት በትግበራ ላይ ይገኛሉ።

3ተኛው ሀገር አቀፍ የዘላቂ ልማት ግቦች ትግበራ የፈቃደኝነት ግምገማ ሪፖርትን የተመለከተ የምክክር መድረክ ሰኔ 2/2017 ዓ.ም መካሄዱ ይታወቃል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ኢትዮጵያ የዘላቂ ልማት ግቦችን ከሀገራዊ የልማት ዕቅዶቿ ጋር በማስተሳሰር በከፍተኛ ኃላፊነት እየተገበረች እንደሆነ ተናግረዋል።

በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ሆና በርካታ የልማት ስራዎችን በማከናወን በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በአካባቢ ጥበቃ ውጤት እያስመዘገበችና ዜጎቿን ተጠቃሚ እያደረገች ነው ብለዋል።

በ3ኛው ሀገር አቀፍ የዘላቂ ልማት ግቦች የፈቃደኝነት ግምገማ ሪፖርት ዝግጅት የተሳተፉት የኢኮኖሚ አማካሪው ዳዊት አየለ፥ ኢትዮጵያ ሪፖርቱን ማዘጋጀቷ ስኬቶችንና ቀሪ ስራዎችን በመለየት ግቦችን ለማሳካት እንድትተጋ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

የግምገማ ሪፖርቱ እስከ ፈረንጆቹ 2030 ድረስ ባሉት አምስት ዓመታት ትኩረት የሚደረግባቸውን ጉዳዮች በመለየት ግቡን ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት ትልቅ መነሻ እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡

በሀገሪቱ የተከናወኑ የዘላቂ ልማት ግቦችን የገመገመ መሆኑን ጠቅሰው፥ ኢትዮጵያ በብዙ መልኩ ትልልቅ ስኬት ማስመዝገቧን ገልጸዋል።

በተለይ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እንዲሁም ዘላቂ ልማትን የማረጋገጥ ተግባር ላይ የተሰሩ ስራዎች ከፍተኛ ውጤት እንደተመዘገበባቸው ጠቁመዋል፡፡

ማህበራዊ አገልግሎትን ከማስፋፋት አንጻር ጤና፣ ትምህርት፣ ውሃ፣ ኤሌክትሪክና ሌሎች ማህበራዊ ልማትን ለሁሉም ህብረተሰብ ለማቅረብ በተከናወኑ ተግባራት ከፍተኛ ዕድገት መምጣቱን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ለግቦች መሳካት አስፈላጊ የሆኑ የፖሊሲ ማዕቀፎችን በመተግበር ስኬታማ መሆኗንም ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት ካጋጠሙ በርካታ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች አንጻር ከ60 በመቶ በላይ ግቦችን በስኬት እየፈጸመች መሆኗ የሚደነቅ ነው ብለዋል።

እስካሁን የተመዘገቡ ውጤቶች በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የዘላቂ ልማት ግቦቹ እንደሚሳኩ አመላካች መሆናቸውን አንስተው፥ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

በተለይ የልጆች ጤና፣ ፍትሐዊ የማህበራዊ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማጠናከር፣የሴቶችና የወጣቶችን እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተጨማሪ እርምጃዎችን መውሰድና ኢንቨስትመንትን ፈሰስ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ለዚህም የባለድርሻ አካላትን፣የህብረተሰቡንና የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ ተጨማሪ ሀብት ማሰባሰብ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ይህን ማድረግ ከተቻለ ኢትዮጵያ ሁሉንም ግቦች በማሳካት በዓለም ላይ ውጤታማ ከሆኑ ሀገራት ተርታ መሰለፍ ትችላለች ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም