የመኖሪያ ቤት ችግርን ለማቃለል በተለያዩ አማራጮች የሚከናወኑ የቤት ግንባታዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2017(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል የሚያግዙ የቤት ግንባታዎች በተለያዩ አማራጮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባዋ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ፣ ጀርመን አደባባይ አካባቢ በመንግስት በጀት በመገንባት ላይ የሚገኙ የመኖሪያ ቤቶች የደረሱበትን ደረጃ ተመልክተዋል።

የቤት ፍላጐት በመንግስት ብቻ ሊመለስ የሚችል ባለመሆኑ በግንባታ ስራ ላይ የተሰማሩ የግል አልሚዎች ግንባታዎቻቸውን ባጠረ ጊዜና በጥራት እንዲያጠናቅቁም ከንቲባዋ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የከተማ አስረተዳደሩም ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት አልሚዎች ግንባታዎቻቸውን በተያዘላቸው ጊዜ እንዲያጠናቅቁ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።




የመኖሪያ ቤት ችግርን ለማቃለል በተሰጠው ልዩ ትኩረት መሰረት በመንግስት፣ በመንግስትና በግሉ ዘርፍ እንዲሁም በግሉ ዘርፍ የግንባታ ፕሮጀክቶች እንዲፋጠኑ እየተደረገ እንደሚገኝ የከንቲባ ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ሚኤሳ ኤለማ(ዶ/ር) ለኢዜአ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም በመንግስት እየተከናወኑ ያሉ የቤት ግንባታ ፕሮጀክቶች እየተፋጠኑ እንደሚገኙ ገልጸው በተመሳሳይ መንግስት ከግሉ ዘርፍ ጋር እያከናወናቸው ያሉት ግንባታዎችም በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

በግሉ ዘርፍ እየተከናወኑ ላሉት የመኖሪያ ቤት ግንባታ ፕሮጀክቶችም መንግስት ከመሬት አቅርቦት ጀምሮ አስፈላጊ ጉዳዮችን በማሟላት እያገዘ በመሆኑ በተሻለ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ እንዳሉ ጠቁመዋል።

ኃላፊው አያይዘውም መሬት አጥረው ይዘው ወደ ተጨባጭ ስራ ያልገቡ የግሉ ዘርፍ የቤት አልሚዎች በፍጥነትና በጥራት ወደ ግንባታ እንዲገቡና የህዝቡን የቤት ፍላጎት እንዲያሟሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም