የአዕምሯዊ ንብረት ውጤቶች ተገቢው ጥበቃ እንዲደረግላቸው መገናኛ ብዙሃን የመረጃ ተደራሽነት ላይ በስፋት ሊሰሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የአዕምሯዊ ንብረት ውጤቶች ተገቢው ጥበቃ እንዲደረግላቸው መገናኛ ብዙሃን የመረጃ ተደራሽነት ላይ በስፋት ሊሰሩ ይገባል
አዲስ አበባ፤ሰኔ 6/2017 (ኢዜአ)፦የአዕምሯዊ ንብረት ውጤቶች ተገቢው ጥበቃ ተደርጎላቸው ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ዕድገት የድርሻቸውን እንዲወጡ መገናኛ ብዙሃን የመረጃ ተደራሽነት ላይ በስፋት መስራት አለባቸው ሲል የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ገለጹ።
ባለስልጣኑ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች አእምሯዊ ንብረት ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር እንዳሉ ሞሲሳ በስልጠናው መክፈቻ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የአእምሯዊ ንብረት ስርዓት ግንባታ ውስጥ የሚዲያ ተቋማት ከፍተኛ ሚና አላቸው።
የአዕምሯዊ ንብረት ውጤቶች ለአገር ልማት የራሱን አስተዋፅኦ እንዲያደርግ በተገቢው መንገድ መተዋወቅና መመዝገብ እንዳለበትም አንስተዋል።
ባለስልጣኑ በፓተንትና ንግድ ምልክት፣በቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ላይ የተለያዩ ስራዎች እየሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በርካታ የአእምሮ ንብረት ፈጠራ ውጤቶች ቢኖራትም የፈጠራ ውጤቶቹን ከማስመዝገብ አኳያ በሚፈለገው ልክ አልተሰራም ብለዋል።
መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያ የምርምርና የፈጠራ ውጤቶች ላይ ተከታታይ ዘገባ በመስራት ለህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ በትኩረት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎቹ በፓተንት ስርዓት፣ በንግድ ምልክት ምንነት ጠቀሜታና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ፣አእምሯዊ ንብረትና ሚዲያ እንዲሁም በቅጂና ተዛማጅ መብቶች ላይ ያተኮሩ ማብራሪያዎች ተሰጥተዋል።
የአእምሯዊ ንብረት ውጤቶች ተገቢው ጥበቃ ተደርጎላቸው ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ዕድገት የድርሻቸውን እንዲወጡ መገናኛ ብዙሃን የመረጃ ተደራሽነት ላይ በስፋት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።