በክልሉ ልማትና እድገትን ለማፋጠን አመራሩ ሚናውን በበለጠ ሊወጣ ይገባል-ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

ባህር ዳር፤ሰኔ 6/2017 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል ልማትና እድገትን ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት አመራሩ ሚናውን በበለጠ ሊወጣ እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ አስገነዘቡ።

"አርቆ ማየት አርቆ መስራት" በሚል መሪ ሃሳብ የአማራ ክልል አሻጋሪ ዕድገትና የልማት ዕቅድ ዙሪያ ለክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የተዘጋጀው የስልጠና መድረክ ዛሬ በባህር ዳር ተጀምሯል።

ርዕሰ መስተዳደር አቶ አረጋ ከበደ በማስጀመሪያ ስነ-ስርአቱ ላይ እንደገለፁት፥በክልሉ ከድህነት ለመላቀቅ የሚያስችል የ25 አመት የፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል።

ከፍኖተ ካርታው የተቀዳና ከ2018 በጀት ዓመት ጀምሮ የሚተገበር የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።

እቅዱን በማሳካት የክልሉን ልማትና ዕድገት ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት አመራሩ ሚናውን በበለጠ ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ ደመቀ ቦሩ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥በክልሉ በየጊዜው የሚከሰቱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ችግሮች ክልሉ ባለው የመልማት ፀጋ ልክ ወደፊት እንዳይራመድ አድርገውታል ብልዋል ።

ከችግሩ በዘላቂነት ለመላቀቅ የሚያስችል እቅድ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።

አመራሩ ስልጠናውን በትኩረት በመከታተል አሻጋሪ የልማት ዕቅዱ እንዲሳካ የላቀ ሚናውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

ዛሬ የተጀመረው የከፍተኛ አመራሮች ስልጠና እስከ ሰኔ 13 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚቆይ የወጣው መርሃ ግብር አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም