በክልሉ ውጤታማ የመንግስት የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓት ተግባራዊ በማድረግ የልማት ስራዎችን ለማፋጠን ትኩረት ተደርጓል-ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ውጤታማ የመንግስት የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓት ተግባራዊ በማድረግ የልማት ስራዎችን ለማፋጠን ትኩረት ተደርጓል-ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ

ጋምቤላ፤ሰኔ 6/2017(ኢዜአ)፦በጋምቤላ ክልል ውጤታማ የመንግስት የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓት ተግባራዊ በማድረግ የልማት ስራዎችን ለማፋጠን ትኩረት መደረጉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።
ክልል አቀፍ የፋይናንስ እና የገቢ ዘርፍ የምክክር መድረክ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
ርዕሰ መስተዳድሯ በምክክር መድረኩ ላይ እንዳሉት፥በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን እውን ለማድረግ የተጠናከረ የፋይናንስ አቅም መገንባት ያስፈልጋል።
ውጤታማ የመንግስት የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓት ተግባራዊ ከማድረግ አኳያም የመንግስት የወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ማሻሻያ ሪፎርም በክልሉ ሲተገበር መቆየቱን አውስተዋል።
በዚሁ መሰረት በበጀት አመቱ በክልሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ስኬታማ ለማድረግም በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን ገልፀዋል።
በተለይም ክልሉ የሚሰበስበው ገቢ ድህነትን በመቀንስና ልማትን በሚያፋጥኑ የልማት ስራዎች ላይ ለማዋል የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ እንደነበሩ ተናግረዋል።
በዚህም የክልሉ የድጎማ በጀትም ሆነ የገቢ አሰባሰብ ሂደቱ እድገት እያሳየ መምጣቱ ለተመዘገቡት ውጤቶች አንዱ ማሳያ መሆኑንም ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ የመንግስትን ውስን በጀት በአግባቡ ጥቅም ላይ ከማዋልና ገቢን በአግባቡ ሰብስቦ ከመጠቀም አንፃር ውስንነቶች መኖራቸውን አንስተዋል።
የዛሬው የምክክር መድረክ አላማም በፋይናንስ አስተዳደር፣አጠቃቀምና በገቢ አሰባሰብ ዙሪያ የሚስተዋሉ ዉስንነቶችን ለመፍታት ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ኡማን ኡጁሉ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፥ ከተለያዩ የሀብት ምንጮች የሚገኘውን በጀት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው የልማት ስራዎች ላይ ለማዋል ጥረት እየተደረገ ነው።
የክልሉን የፋይናንስ ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ከክልል ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር ለማጠናከር እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
የምክክር መድረኩ በፋይናንስና በገቢ ዘርፍ የተደረጉ ማሻሻያዎች አተገባበርን በመገምገም በቀጣይ የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በምክክር መድረኩ ላይ የክልል፣የዞንና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የዘርፉ ከፍተኛ ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ናቸዉ።