ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም ነባራዊ ሁኔታ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ዘርፈ ብዙ የዲፕሎማሲ ስራዎችን ማጠናከር ይገባል- አምባሳደር ሃደራ አበራ

አዲስ አበባ፤ሰኔ 6/2017 (ኢዜአ)፦ተለዋዋጭና ኢ-ተገማች በሆነው የዓለም ነባራዊ ሁኔታ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ዘርፈ ብዙ እና የተደራጁ የዲፕሎማሲ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሃደራ አበራ ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የውጭ ጉዳይ ኢኒስቲትዩት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር በመተባበር ለወዳጅነት ቡድኖችና ፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባላት ያዘጋጀው ስልጠና ተጀምሯል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሃደራ አበራ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ሀገራዊ ልማትና ብልጽግናን እውን ለማድረግ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም የውጭ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ አጋርነትን ለማጠናከር፣ገጽታ ለመገንባት፣ የዜጎችን ጥቅም ለማስከበር እና የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ሁሉም አካላት በጋራ መረባረብ አለባቸው ብለዋል።

ተለዋዋጭና ኢ-ተገማች በሆነው የዓለም ነባራዊ ሁኔታ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ዘርፈ ብዙ እና የተደራጀ የዲፕሎማሲ ስራ ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለዚህ ደግሞ የዓለም ፖለቲካዊ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስርዓቱ የሚጠይቀውን የውጭ ግንኙነት ስልት መንደፍና መከተል፤የዓለም አስቻይ ሁኔታዎችን በጥንቃቄ በማየት በአስተውሎት መራመድ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች መሆኑን ገልጸው፤የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብሩ ስትራቴጂያዊ አጋሮች የማብዛት ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ብሔራዊ ጥቅሟን ማስጠበቅ የሚያስችሉ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸው፣ በመርህ ላይ የተመሰረተ ዓለም አቀፋዊ እና ቀጣናዊ አጋርነትን ማሳድግ ወሳኝ መሆኑን አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ፣ የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት፣የአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት፣ እንዲሁም የብዝሀ ብሔር መገኛ መሆኗን በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራችን መግለጽና ገጽታዋን መገንባት ይጠበቅብናል ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ መንግስት ከሚሰራው የውጭ ግንኙነት ስራ ባሻገር በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም