ባህር ዳር ከተማ በወንደሰን በለጠ ሀትሪክ ታግዞ ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል - ኢዜአ አማርኛ
ባህር ዳር ከተማ በወንደሰን በለጠ ሀትሪክ ታግዞ ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2017 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ34ኛ ሳምንት ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ ወላይታ ድቻን 4 ለ 0 አሸንፏል።
ማምሻውን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ አጥቂው ወንደሰን በለጠ በ49ኛው፣ 64ኛው እና 67ኛው ደቂቃ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ሀትሪክ ሰርቷል።
ወንደሰን በለጠ በ20ኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር ባህር ዳር ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስን 4 ለ 1 ባሸነፈበት ጨዋታ ላይም ሀትሪክ መስራቱ የሚታወስ ነው።
ተጫዋቹ በሁለቱም ጨዋታዎች ላይ ሀትሪክ የሰራው በሁለተኛው 45 ባስቆጠራቸው ግቦች መሆኑ አጋጣሚውን የተለየ ያደርገዋል።
ፍጹም ዓለሙ ቀሪዋን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ውጤቱን ተከትሎ ባህር ዳር ከተማ በሊጉ ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል። ሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቡድኑ ነጥቡን ወደ 51 ከፍ አድርጓል።
በአንጻሩ በሊጉ 11ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ወላይታ ድቻ በ45 ነጥብ 8ኛ ደረጃን ይዟል።
ቀን ላይ በተደረገ ጨዋታ ሲዳማ ቡና እና ድሬዳዋ ከተማ አንድ አቻ ተለያይተዋል።
ጨዋታዎቹን ተከትሎ የ34ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ተጠናቋል።
የ35ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ከሰኔ 7 ቀን 2017 ዓ.ም አንስቶ ይካሄዳል።