በህንድ የአውሮፕላን አደጋ የ204 ዜጎች ህይወት አልፏል- የሕንድ ፖሊስ - ኢዜአ አማርኛ
በህንድ የአውሮፕላን አደጋ የ204 ዜጎች ህይወት አልፏል- የሕንድ ፖሊስ

አዲስ አበባ፤ሰኔ 5/2017 (ኢዜአ)፦በህንድ የአውሮፕላን አደጋ የ204 ዜጎች ህይወት ማለፉን የሀገሪቷ ፖሊስ አስታወቀ።
በሕንድ 242 መንገደኞችን ይዞ በህንድ ሰሜን ምዕራባዊ ክፍል አህመዳባድ ከተማ ከሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ለንደን ጋትዊክ ለማምራት በተነሳበት ቅፅበት በአካባቢው በሚገኝ ሆስፒታል የህክምና ባለሙያዎች ማረፊያ ላይ ተከስክሷል።
በቦይንግ 787-8 ድሪምላይነር አውሮፕላን ውስጥ 169 ህንዳውያን፣ 53 የብሪታኒያ ዜጎች፣ 7 ፖርቹጋላዊ እና አንድ ካናዳዊ ነበሩ።
በአደጋው የተረፈ ሰው ለማግኘት የሚቻልበት እድል እጅጉን የጠበበ ነው ሲል የአህመዳባድ ፖሊስ ኃላፊ ለአሶሲዬትድ ፕሬስ ገልጾ ነበር።
ይሁንና ማምሻውን በወጣ መረጃ የ40 ዓመት የህንድ እና ብሪታኒያዊ ጥምር ዜግነት ያለው ቪሽዋሽ ኩማር ራሜሽ ከአደጋው መትረፉ ተጠቁሟል።
እስከ አሁን የ204 ሰዎች አስክሬን ተገኝቷል።
የአውሮፕላኑ አካል የህክምና ባለሙያዎች ማረፊያ ላይ ወድቆ ቢያንስ አምስት የህክምና ተማሪዎች መሞታቸውን እና 50 ገደማ የሚሆኑት መጎዳታቸው ተገልጿል።
የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት የሀዘን መግለጫ መልዕክት አደጋው ቃል ከሚገልጸው በላይ ልብ የሚሰብር ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በአደጋው ለተጎዱ በሙሉ ልባዊ ሀዘናቸውን በመግለጽ መጽናናትን ተመኝተዋል።