የሙሉጌታ ከበደ የቀብር ስነ ስርዓተ ተፈጸመ - ኢዜአ አማርኛ
የሙሉጌታ ከበደ የቀብር ስነ ስርዓተ ተፈጸመ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2017 (ኢዜአ)፦ የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቂ ሙሉጌታ ከበደ የቀብር ስነ ስርዓት ዛሬ ኮልፌ በሚገኘው የሙስሊም መካነ መቃብር ተፈጽሟል።
በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች፣ የአሁን እና የቀድሞ እግር ኳስ ተጫዋቾች፣ የእግር ኳስ አፍቃሪያን፣ ቤተሰቦቹ እና ወዳጆቹ ተገኝተዋል።
ከስርዓተ ቀብሩ በፊት ዛሬ ማለዳ በአዲስ አበባ ስታዲየም የክብር ሽኝት ተደርጎለታል።
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በጨራሽ አጥቂነቱ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ሙሉጌታ ከበደ በ1959 ዓ.ም በደሴ ከተማ የተወለደ ሲሆን በእግር ኳስ ቆይታው ለደሴ ከተማ ከፍተኛ ሁለት፣ ለወሎ ፔፕሲ፣ ለወሎ ምርጥ፣ ለቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ለአዲስ አበባ ምርጥና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫውቷል።
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለረጅም ጊዜያት በቋሚነት በመሰለፍ ከ90 በላይ ጎሎችን አስቆጥሯል።
ሙሉጌታ ከበደ በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ትናንት ህይወቱ ማለፉ ይታወቃል። የቀብር ስነ ስነ ስርዓቱ ዛሬ ኮልፌ በሚገኘው የሙስሊም መካነ መቃብር ተፈጽሟል።
ሙሉጌታ ባለ ትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነበር።