ፊንላንድ በተለያየ መስክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን አጋርነት ታጠናክራለች - የፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤሊና ቫልቶነን - ኢዜአ አማርኛ
ፊንላንድ በተለያየ መስክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን አጋርነት ታጠናክራለች - የፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤሊና ቫልቶነን

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2017(ኢዜአ)፦ፊንላንድ በተለያየ መስክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን አጋርነት እንደምታጠናክር የፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤሊና ቫልቶነን ተናገሩ።
ፊንላንድ ለስምንት ተከታታይ ዓመታት በዓለም ቁጥር አንድ የደስተኞች አገር በመባል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተሰይማለች።
ይህን መነሻ በማድረግ በሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋባዥነት የአፍሪካ ጋዜጠኞች በቅርቡ በፊንላንድ ጉብኝት አካሂደዋል።
በዚህ ወቅት የፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤሊና ቫልቶነን ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ፊንላንድና ኢትዮጵያ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው አገራት ናቸው።
ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዘርፈ-ብዙ ግንኙነት ማጠናከር እንደምትፈልግ የገለጹት ሚኒስትሯ በተለይም በልማት፣ በንግድና ኢንቨስትመንት መስኮች የበለጠ ትኩረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያና የፊንላንድ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከተመሰረተ 66 ዓመታትን አስቆጥሯል።
ሁለቱ ሀገራት ለረጅም ዓመታት የቆየ በጋራ ጥቅምና መተማመን ላይ የተመሰረተ የሁለትዮሽ ግንኙነትም አላቸው።
የልማት ትብብራቸው በትምህርት፣ በገጠር ልማት፤ በንግድና ኢንቨስትመንት እና በሌሎችም መስኮች ላይ ያተኮረ ነው።
ይህ ዘርፈ-ብዙ የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ያድጋል የሚል እምነት እንዳላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኤሊና ቫልቶነን ተናግረዋል።
በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ኮሙኒኬሽንስ ጉዳዮች አምባሳደር አን ላሚላ በበኩላቸው ለኢዜአ እንደገለጹት የሚዲያ ጉብኝቱ ዓላማ ስለ ፊንላንድ ማሳወቅና የስኬት ምስጢሮችን ማካፈል ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ማሳደግ ጭምር ነው።
ፊንላንድ ከአፍሪካ ሕብረት፤ በተናጥልም ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ጋር ስትራቴጂክ አጋርነት እንዳላት የገለጹት አምባሳደሯ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነትም ጠንካራ መሰረት ያለው መሆኑን አስታውሰዋል።
የደስተኛ ህዝቦች መኖሪያ የምትሰኘው ፊንላንድ ግብር ከፋይ የአገሪቱ ዜጎች በታማኝነትና በደስታ ግብር የሚከፍሉባት ሰሜን አውሮፓዊት ሀገር ነች።
በትምህርት፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በጾታ እኩልነት፤ እንዲሁም በጤናና ለማህበረሰብ ምቹ ቤተሰብ መፍጠርን ጨምሮ ባከናወነቻቸው ጠንካራ የማህበራዊ ደህንነት ትስስር ስራዎች ዜጎቿ ደስተኞች መሆናቸው ይገለጻል።