አርሜኒያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ታሪካዊ ወዳጅነት ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ትሰራለች - ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቫሃን ኮስታንያን

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2017(ኢዜአ)፦ አርሜኒያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ታሪካዊ ወዳጅነት ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደምትሰራ የአርሜኒያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቫሃን ኮስታንያን ገለጹ።

የአርሜኒያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቫሃን ኮስታንያን እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያና አርሜኒያ ታሪካዊና ጠንካራ የሁለትዮሽ ወዳጅነት አላቸው።

በአራተኛው ክፍለ ዘመን የተጀመረው የኢትዮጵያና አርሜኒያ ግንኙነት እያደገና ዘላቂ ወዳጅነት እያስመዘገበ እንደሚገኝ ገልጸዋል። 

በአዲስ አበባ የሚታየው የአርሜኒያ ህዝቦች አሻራም የሁለቱን ሀገራት የህዝብ ለህዝብ ጥልቅ ወዳጅነት የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚገኙት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የአርሜኒያ ማህበረሰብም በአዲስ አበባ በንግድና በዕደ-ጥበብ  ሙያ በመሰማራት ከኢትዮጵያዊያን ጋር በጥብቅ ወዳጅነትና አብሮነት እየኖሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ የአርሜኒያዊያን የስራ ባህል ውርስ የሆኑ ጌጣ ጌጦች፣ ኪነ-ጥበበኞች፣ ነጋዴዎችና የተለያዩ የሙያ ጠበብቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያና አርሜኒያ መካከል አንዳቸው ለአንዳቸው ቅርብ አጋር የሚሆኑበት ከፍተኛ ዕድል መኖሩን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክለዋል።

የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውም የኢትዮ-አርሜንያን ህዝቦች የባህል፣ የትምህርት፣ ቴክኖሎጂና የጤና መስክ የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው አብራርተዋል።

ለአብነትም በኢትዮ-አርሜኒያን መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር የሳይንስ፣ የባህልና ትምህርት ስምምነት መፈረሙን አስታውሰዋል።

በቀጣይም የጋራ የመንግስታት ኮሚሽን በማቋቋም የፖለቲካና ሌሎች የትብብር መስኮችን ለማጠናከር የሃሳብ ልውውጥ መደረጉን አስረድተዋል። 

በኢትዮጵያ ቆይታቸውም ፖለቲካዊ ምክክር፣ ቀጣናዊ፣ አፍሪካዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን የዳሰሰ መሆኑን አስረድተዋል። 

በምክክር መድረኩም ኢትዮጵያና አርሜኒያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅትና በሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት አባልነታቸውን በመጠቀም ያላቸውን የነቃ ተሳትፎ ለማጠናከር አጽንኦት እንደተሰጠ አብራርተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም