የሀይማኖት ተቋማት በዘላቂ ሰላም ግንባታ ሂደት ሚናቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የሀይማኖት ተቋማት በዘላቂ ሰላም ግንባታ ሂደት ሚናቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል
ባህርዳር ሰኔ 5/2017( ኢዜአ):- የሀይማኖት ተቋማት በዘላቂ ሰላም ግንባታ ሂደት ያላቸውን ጉልህ ሚና አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) አስታወቁ።
በባህርዳር ከተማ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው 3ኛው ዙር የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ሀገር አቀፍ የሰላም ጉባኤ ተጠናቋል።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሃይማኖት አባቶች ለተከታዮቻቸው ሰላምን አብዝተው ሊሰብኩ ይገባል።
የሀይማኖት ተቋማት በዘላቂ ሰላም ግንባታ ሂደት ሚናቸው የጎላ መሆኑን ጠቁመው ተቋማቱ በዘርፉ እየተወጡ ያለውን ሚና አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤም ሰላምን ለማስፈንና አፅንቶ ለማዝለቅ የጀመረውን የሰላም ጉባኤ በቀጣይም አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል ።
“በተለያዩ አካባቢዎች እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች ከዕምነትና እሴቶቻችን ጋር አብረው የማይሄዱ መሆናቸውን ተገንዝበን ችግሮቻችንን ቁጭ ብለን በመነጋገርና በመመካከር በመፍታት ሰላምን ማፅናት ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል” ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል ።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንትና የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ በበኩላቸው “ፈተናዎች እየተከሰቱ ያሉት በሰው ሰራሽ መንገድ ነው” ብለዋል።
ከፈተናዎች ለመውጣት ከግጭትና መሰል ተግባራት መራቅ እንደሚገባ ጠቁመው ችግርን በሰለጠነ አግባብ በመፍታት የሀገርን ሰላምና አንድነት ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል ።
“ሰላምን ለማምጣት ሁላችንም አንድ ሆነን ግጭቶችን ማስቀረት አለብን” ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያሪክ አቡነ ማትያስን በመወከል መልዕክት ያስተላለፉት የባህርዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል አቡነ አብርሃም ናቸው።
“ ከክፉ ነገር በመራቅ ለዘላቂ ሰላም መስፈን ህዝባችንን ተግተን ስለሰላም ማስተማር አለብን” ብለዋል።
አለመግባባትን በሰላማዊ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ በንግግርና በውይይት መፍታት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ፀሀፊ ቄስ ደረጀ ጀንበሩ በበኩላቸው “አሁን እየታየ ያለው ሰላም እንዳይጠፋ ከስሜታዊነት በራቀ መንገድ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን በመፍታት ዘላቂ ስላም ማስፈን ይገባል” ብለዋል ።
“በውይይትና በንግግር ችግሮችን በመፍታት ለዘላቂ ሰላም መስፈን ልንተጋ ይገባል “ ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የባህርዳርና የደሴ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ አቡነ ልሳነ ክርስቶስ ናቸው ።
የሰላም ጉባኤው እንዲሳካና በሰላም እንዲጠናቀቅ አስተዋጾ ላደረጉ አካላት የምስጋና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።