አዲስ ተሿሚ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አመራሮች ሀገራዊ ተልዕኳቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል-ምክር ቤቱ - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ ተሿሚ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አመራሮች ሀገራዊ ተልዕኳቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል-ምክር ቤቱ

አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 5/2017(ኢዜአ)፦ አዲስ ተሿሚ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አመራሮች ሀገራዊ ተልዕኳቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።
ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 36ኛ መደበኛ ስብሰባ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ምክትል ሰብሳቢ እና የሥራ አመራር ቦርድ አባላትን ሹመት በሁለት ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።
በዚህም አቶ ተስፋዬ ንዋይን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ እንዲሁም አቶ ተክሊት ይመስል እና ወይዘሮ ነሲም አሊን የሥራ አመራር ቦርድ አባላት አድርጎ ሹሟል።
የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጅጌ (ዶ/ር) የቀረቡ እጩዎችን በተመለከተ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ተጠሪ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ተሿሚዎቹ በህገ መንግስቱ መሰረት የሚደረጉ ምርጫዎችና ህዝበ ውሳኔዎች በፍትሐዊነትና ገለልተኝነት ማስፈጸም የሚችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ተሿሚዎች የትምህርት ዝግጅታቸውና ከዚህ በፊት በፍትሕ ዘርፉ የሰሩባቸው የሥራ ልምዶችና የነበራቸው አፈፃፀም ኃላፊነታቸውን በብቃት እንደሚወጡ ማሳያዎች ናቸው ብለዋል፡፡
ቀደም ብሎ ሥራውን በጥራትና በብቃት ማከናወን የሚችሉ መልማይ ኮሚቴዎች ተለይተው ከህዝብ፣ ከሲቪክ ማህበራትና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጥቆማ ተቀብለው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡
ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራርና አባላት ጋር ምክክር መደረጉን ገልጸው፤ ተሿሚዎቹ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተዓማኒነቱን አስጠብቆ እንዲቀጥል የሚያስችሉና የማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባል ያልሆኑ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ተጠሪ ሚኒስትሩ አክለውም የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ሆነው የተሾሙት አቶ ተስፋዬ ንዋይ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት እና የፌደራል ፍርድ ቤቶች ቃል አቀባይ ሆነው ስራቸውን በብቃት ማከናወናቸውን አውስተዋል፡፡
የሥራ አመራር ቦርድ አባል ሆነው የተሾሙት አቶ ተክሊት ይመስል የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት እንዲሁም ወይዘሮ ነሲም አሊ የሀረሪ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ በመሆን ውጤታማ ሥራ ማከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፤ ተሿሚዎቹ ከዚህ በፊት ያላቸው ልምድ ገለልተኛ ሆነው መሥራት እንደሚችሉ እንደሚያሳይ ተናግረዋል፡፡
የማንኛውም ፖለቲካ ድርጅት አባል አለመሆናቸውና በሙያቸው ምስጉን መሆናቸው ሀገርና ትውልድን የሚያሻግር ሥራ እንደሚሰሩ እምነት እንዲኖረን አድርጓል ነው ያሉት፡፡
ተሿሚዎች በምክር ቤቱ የተሰጣቸውን ሀገራዊ ኃላፊነት በብቃት መወጣት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ሹመት በውሳኔ ቁጥር 10/2017 በአብላጫ ድምፅ መጽደቁን አስታውቀዋል፡፡
ምክር ቤቱ በስብሰባው የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅን ለሰው ሀብት ልማት ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም የዕፅዋት ጥበቃ እና ኳራንታይን ረቂቅ አዋጅን ለግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ መርቷል።