የሸገር ከተማ የመኖሪያ ብቻ ሳይሆን የማምረቻ ከተማ እንዲሆን በተከናወኑ ስራዎች ውጤት እየተገኘ ነው - ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የሸገር ከተማ የመኖሪያ ብቻ ሳይሆን የማምረቻ ከተማ እንዲሆን በተከናወኑ ስራዎች ውጤት እየተገኘ ነው - ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2017(ኢዜአ)፡- የሸገር ከተማ የመኖሪያ ብቻ ሳይሆን የማምረቻ ከተማ እንዲሆን በተከናወኑ ስራዎች ውጤት እየተገኘ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) ተናገሩ።
በሸገር ከተማ አስተዳደር መነ አቢቹ ክፍለ ከተማ የአፕል ችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር የአስተዳደሩ አመራሮች፣ የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት እና ነዋሪዎች በተገኙበት ተካሄዷል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር)፣ ከተማው ከተመሰረተ ጀምሮ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም ከተማዋ የመኖሪያ ብቻ ሳትሆን የማምረቻ ማዕከል እንድትሆን ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።
ከተማውን የዘመናዊ ግብርና ማዕከል ለማድረግ ባለፉት ዓመታት ከ10 ሺህ በላይ የማምረቻ ሼዶች ተገንብተው ለበርካታ ሰዎች የስራ እድል መፈጠሩን ገልጸዋል።
በሼዶቹ ውስጥ ሰፋፊ የዶሮ እርባታ ስራዎች፣ የወተት ላሞች እርባታ፣ በስጋ እንስሳት ማድለብና በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ውጤታማ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
በተያዘው ክረምትም በከተማ አስተዳደሩ በ1 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የአፕልና አቮካዶ ችግኝ እንደሚተከል ገልጸው ዛሬም በመነ አቢቹ ክፍለ ከተማ በ38 ሄክታር መሬት ላይ የአፕል ችግኝ መተከሉን ተናግረዋል።
የሸገር ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የግብርና ክላስተር አስተባባሪ አቶ ግርማ ሀይሉ፣ በከተማ አስተዳደሩ ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።
በዚህ ክረምትም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዝና ለውጭ ገበያ የሚውሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች ይተከላሉ ብለዋል።
ከሚተከሉት የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች መካከል ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው የአፕል ችግኝ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የሸገር ከተማ አስተዳደር መነ አቢቹ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ሆርዶፋ በበኩላቸው በክፍለ ከተማው በዚህ ክረምት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል አስፈላጊ ዝግጅቶች መደረጋቸውን ተናግረዋል።
በክፍለ ከተማው በአጠቃላይ በ50 ሄክታር መሬት ላይ ከ50 ሺህ በላይ የአፕል ችግኝ ተከላ መጀመሩን ገልጸው የአካባቢው አርሶ አደርም መልካም ተሞክሮ እየወሰደ የተተከለውን ችግኝ እንዲንከባከብም አሳስበዋል።
በችግኝ ተከላው ላይ ከተሳተፉ የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አቶ መስፍን መላኩ፣ በክረምቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
በተከላው ተሳትፎ ያደረጉት የአፕል ችግኝ ጠቀሜታው ትልቅ መሆኑን በመገንዘብ መሆኑን ተናግረው በአካባቢው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ሊጠናከር እንደሚገባም አመልክተዋል።