ሰራዊቱ የሀገርን ሉዓላዊነት በማስጠበቅ አለኝታነቱን አስመስክሯል - ኢዜአ አማርኛ
ሰራዊቱ የሀገርን ሉዓላዊነት በማስጠበቅ አለኝታነቱን አስመስክሯል

አሶሳ፤ ሰኔ 5/2017(ኢዜአ):- ሰራዊቱ የሀገርን ሉዓላዊነት በማስጠበቅ አለኝታነቱን አስመስክሯል ሲሉ የመከላከያ ሰራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ገለጹ።
በቴክኖሎጂ የበለጸገና ለሌሎች ሀገራትም ምሳሌ የሚሆን መከላከያ ሰራዊት መገንባቱንም አክለዋል።
በምዕራብ ዕዝ የ404ኛ ህዳሴ ኮር 3ኛ ዓመት የምስረታ በዓል "ህዳሴን በህዳሴ" በሚል መሪ ሃሳብ በአሶሳ ከተማ በፓናል ውይይት ተከብሯል።
በመድረኩ 404ኛ ህዳሴ ኮር የአካባቢውን ሠላም በማስጠበቅ ረገድ እና በልማት ስራዎች ላይ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ በተመለከተ በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ መምህራን የመነሻ ጽሁፍ ቀርቧል።
በመድረኩ የተገኙት የመከላከያ ሰራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ እንደተናገሩት ሰራዊቱ የሀገርን ሉዓላዊነት በማስጠበቅ አለኝታነቱን አስመስክሯል።
በቴክኖሎጂ የበለጸገና ለሌሎች ሀገራትም ምሳሌ መሆን የሚችል ሰራዊት እየተገነባ መሆኑንም አንስተዋል።
ኮሩ በአካባቢው የነበረው የፀጥታ ችግር እንዲቀረፍ ከከፈለው መስዋዕትነት ባለፈ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በአስተማማኝ ሁኔታ ግንባታው እንዲከናወን አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል።
ሰራዊቱ ከመደበኛ ተልዕኮው በተጨማሪ በሰብዓዊ ድጋፍ የሀገር አለኝታነቱን እያስመሰከረ መሆኑን ጠቁመው በደም ልገሳ፣ በአካባቢ ጥበቃናና በሌሎች ተግባራት እያደረገ ያለው ተሳትፎ የህዝብ ወገንተኝነቱን ያረጋገጠበት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጌታሁን አብዲሳ በበኩላቸው፤ ሰራዊቱ በሀገሩ የማይደራደር፣ የሀገር ኩራት እና በሰብዓዊ ድጋፎች ረገድ ጠንካራ ተሳትፎ እያደረገ ያለ ሰራዊት ነው ብለዋል።
ክልሉ በሙሉ አቅሙ ፊቱን ወደ ልማት ስራዎች እንዲያዞር የምዕራብ ዕዝ ሠላምን በማስጠበቅ አኩሪ ገድል መፈጸሙን ጠቁመዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ኢብራሂም አዙቤር እና ፍቃዱ አማረ ሰራዊቱ በክልሉ ለተገኘው ሠላም ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ህብረተሰቡም ለሰራዊቱ ያለው ክብር ከፍተኛ ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ የሀገርን ሠላምና የህዝቦችን አንድነት ማስጠበቅ ላይ አበርክቶው የጎላ መሆኑን አንስተዋል።
በመድረኩ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጌታሁን አብዲሳ፣ የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አስካለች አልቦሮ፣ በብልፅግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢስሃቅ አብዱልቃድር፣ በምዕራብ ዕዝ የ404ኛ ህዳሴ ኮር አዛዥ ኮሎኔል ንጉሴ ለውጤ፣ የሰራዊቱ አመራሮች፣ የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሰራዊት አባላት፣ የተለያዩ የፀጥታ አካላት በተገኙበት በፓናል ውይይት እየተከበረ ይገኛል።