ለሰላምና አብሮነት መጠናከር ጥረታችንን እንቀጥላለን - የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለሰላምና አብሮነት መጠናከር ጥረታችንን እንቀጥላለን - የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተሳታፊዎች
ባህርዳር፤ ሰኔ 5/2017(ኢዜአ)፦ ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥና ለአብሮነት መጠናከር ጥረታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ያለው 3ኛው የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ሀገር አቀፍ የሰላም ጉባኤ ተሳታፊዎች ገለፁ።
3ኛው የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ሀገር አቀፍ የሰላም ጉባኤ ‘‘ኃማኖቶች ለሰላም፣ ለመከባበርና ለአብሮነት’’ በሚል መሪ ሃሳብ ከትላንት ጀምሮ በባህርዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ፀሀፊ ቄስ ደረጀ ጀንበሩ ለኢዜአ እንደገለጹት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አለመግባባቶች ወደ ግጭት እንዳያመሩ አበክሮ እየሰራ ነው።
የሃይማኖት ተቋማት ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ህዝቡ የበኩሉን እንዲያበረክት እያስተማሩ መሆኑን ጠቁመው ግጭቲችንና አለመግባባቶችን በማስቆም የቀደመ አብሮነትን ለማጠናከር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላኛው የሰላም ጉባኤው ተሳታፊ ሊቀ ማዕምራን ሀዲስ ጤናው በበኩላቸው ሰላም ለሰው ልጆች ከምንም በላይ አስፈላጊ በመሆኑ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመነጋገር ከመሰረቱ እንዲቀረፉ ዝቡን እናስተምራን ብለዋል።
የጋራ የሆነ አስተሳሳሪ ትርክትን በመገንባት ችግርን በንግግርና በውይይት ለመፍታት እንደሚሰሩ የገለጹት ደግሞ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን የመጡት የሀገር ሽማግሌ እያሱ ገጃቦ ናቸው።
ሁሉም ተባብሮና ተቀናጅቶ ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ በጋራ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ፀኃፊ ሀጂ መስዑድ አደም በበኩላቸው የሃይማኖት አባቶች ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ለተከታዮቻቸው ሊያስተምሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።