የሲዳማ ክልል ምክር ቤት የአቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስን ያለመከሰስ መብት አነሳ

ሀዋሳ፤ ሰኔ 5/2017(ኢዜአ)፦ የሲዳማ ክልል ምክር ቤት የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊን አለማየሁ ጢሞቲዎስን ያለመከሰስ መብት አነሳ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 6ኛ ዙር 4ኛ የስራ ዘመን 2ኛ አስቸኳይ ጉባኤ ነው የምክር ቤት አባሉን ያለመከሰስ መብት ያነሳው።

የሲዳማ ክልል ፍትህ ቢሮ ሃላፊ ማቶ ማሩ በሙስና ወንጀል፣ ስልጣንን አለአግባብ በመጠቀም፣ በህገ ወጥ ንግድና መሳሪያ ዝውውርና በአደንዛዥ እጽ ዝውውር ማስፋፋት የተጠረጠሩትን አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ማብራሪያ ነው ምክር ቤቱ ተቀብሎ ከተወያየ በኋላ በሙሉ ድምጽ ያጸደቀው።

ምክር ቤቱ በተጨማሪም የሲዳማ ብሮድካስት ኮርፖሬሽንን ስያሜ ለመቀየር በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቷል።

በዚህም መሰረት የሲዳማ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ስያሜ እንዲቀየር የቀረበው ረቂቅ አዋጅ በምክር ቤት አባላት ተቀባይነት አላገኘም።

በዚህም የቀረበው ረቂቅ አዋጅ እንደገና በጥናት ተደግፎ እንዲቀርብ ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ምክር ቤቱ በአስቸኳይ ጉባኤው በሁለት አጀንዳዎች ላይ በጥልቀት ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም