በሚቀጥሉት አሥር ቀናት በተለይም በምዕራብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች የተሻለ ርጥበት ይኖራቸዋል - ኢንስቲትዩቱ - ኢዜአ አማርኛ
በሚቀጥሉት አሥር ቀናት በተለይም በምዕራብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች የተሻለ ርጥበት ይኖራቸዋል - ኢንስቲትዩቱ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2017(ኢዜአ)፦ በሚቀጥሉት አሥር ቀናት በተለይም በምዕራብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች የተሻለ የርጥበት ሁኔታ እንደሚኖራቸው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ በሚቀጥሉት አስር ቀናት የሚኖረውን የአየር ትንበያ አስመልክቶ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በሚቀጥሉት ቀናት የሚኖረው የአየር ሁኔታ ለእርሻ ስራ እንቅስቃሴ በአመዛኙ አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው አመላክቷል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ በምዕራብ እና በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚጠበቀው ከባድ ዝናብ ለወቅቱ የእርሻ ስራ እንቅስቃሴ በአመዛኙ አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረውም ጠቁሟል።
ሆኖም ሊኖሩ የሚችሉ ተያያዥ ስጋቶችን ለመቀነስና የሚኖሩትን መልካም አጋጣሚዎች ለመጠቀም የቀረቡትን የግብርና ሚቲዎሮሎጂ ምክረ ሀሳቦች በሁሉም ደረጃ በተገቢው ሁኔታ መተግበር እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል።
በቀጣዮቹ ቀናት የሚኖረውን የአየር ሁኔታ የተመለከተው ትንበያ ለክረምት ዝናብ መፈጠር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ከቀን ወደ ቀን እየተስፋፉና እየተጠናከሩ እንደሚሄዱ ያሳያል ነው ያሉው።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም፣ በምዕራብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተሻለ የዝናብ መጠንና ሥርጭት እንደሚኖራቸው የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ ሲልም ገልጿል።
በዚህም ርጥበታማው የአየር ሁኔታ በተለይም በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ፣ በሰሜን ምዕራብና በመካከለኛዉ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ በመጠንም ሆነ በሥርጭት እየተስፋፋ ከመሄዱ ጋር ተያይዞ ብዙ ቦታዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው ተጠቁሟል።
ጥቂት ስፍራዎቸ ላይ ደግሞ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች አመላክተዋል ነው ያለው።
በሚቀጥሉት ቀናቶች ከሚጠናከሩት የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ላይ በመነሳት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ብዙ ቦታዎቻቸውን የሚሸፍን ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ነው መረጃው ማመላከቱንም አስታውቋል።
በተጨማሪም አልፎ አልፎ በውሃ አካላትና በካባቢ አየር ውስጥ ከሚጠናከሩት የሚቲዎሮሎጂ ገጽ ላይ በመነሳት በምዕራብ እና በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች በ24 ሠዓት ውስጥ ከ30 ሚሜ በላይ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች አመላክተዋል ብሏል።
በቀጣይ አስር ቀናት የክረምት ወቅት መጀመሩን ተከትሎ በአብዛኛው ርጥበት ተጠቃሚ በሆኑ ተፋሰሶች ላይ ከመጠነኛ እስከ ከፍተኛ የሆነ የገፀ ምድር የውሃ ፍሰት እንደሚኖራቸው ይጠበቃል ሲልም ገልጿል።
የሚኖረውን አዎንታዊ የርጥበት ሁኔታ በአግባቡ ለመጠቀምና አሉታዊ ሁኔታን ለመቀነስ የውሃ ማንጣፈፍያ እና የጎርፍ መቀልበሻ ቦዮችን ማዘጋጀት እንደሚገባም ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።